Saturday, September 28, 2019

From our file: "የኢትዩጵያና የግብጽ ታሪካዊ መፈራት እስከመቼ? መተማመንስ ለምን ይዘገያል?"

(Editor's note: The following historical review might sound, at least in part, a fictionalized narrative or simply a superstitious story. The other way to look at it is as a national myth because it appears an inspiring narrative about our country's past and the vision of its leaders that reigned over the centuries. Such myths collectively known as national mythos have often served nations as national symbols of unity to affirm a set of common shared values. A country like ours fractured by over-dramatization of ethnic differences needs recognition of such national mythos to reinvigorate and strengthen our unity. Most states in Africa who have no serious problem of conflict on ethnic lines threatening their unity have national folklore which includes a founding myth such as the struggle against colonialism or a war of independence. Some of our national myth is spiritual in tone and refer to the Bible, but we have more myths to discover and promote. Abay with our rulers’ desire to build dam on it was definitely a national myth we should accept and re-tale as widely and as frequently as possible.)
_________________________________________________________


                               By Entoto Foum for Social Justice staff writer


በእውቁ የአፄ ምንሊክ ታሪክ ዘጋቢ ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ (1) ተጽፈው ወደ ፈረንሣይኛ ተተርጉመው ከታተሙት ሶስት ቅጽ መጽሃፍት ውስጥ የመጀመሪያው ቅጽ ስለ አባይ ወንዝ ወደ ግብጽ ከመፍሰስ መገደብ በሚተርከው ክፍል የሚከተለው በመግቢያነት ሰፍራል።




"የግብጽ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን በኃይል በማሳደዳቸው የኢትዩጵያ ንጉስ የነበረው ዳዊት እስከ ሴናር (2) ድረስ በመሄድ የግብፅ ክርስቲያኖችን ከመሳደድ አዳናቸው። ይህን በጎ ድጋፍ ለማመስገን ጌታችን መድሃኒታችን የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ከእየሩሳለም ወደ ኢትዩጵያ ተላከ።"


1. የዓለም ክርስቲያኖችና የግብጽ ሙስሊሞች ግጭት፤


ከላይ የተጠቀሰው የጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ መግቢያ በዚያው በመጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚከተለው ተስፋፍቶ ቀርቧል።


በአረቦችና በበርበሮች ፍለሳ እንዲሁም የሃገሪቱ ነባር (Indigenous) ሕዝቦች በብዛት እስልምናን በመቀበላቸው ቁጥራቸው በጣም እየበረከተ የመጣው የግብጽ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን በሃይል ማሳደድ ያዙ። (3) በተለይም የኮንስታቲኖፕል (4) የእየሩሳለም እና የሶርያ ክርስቲያኖች ብዙ ተጎዱ። በዚህ የተከፉት የሮማ (5) እና የፈረንጅ አገር (የአውሮፓ) ክርስቲያኖች በአንድነት ከመከሩ በሗላ ለኢትዩጵያው ንጉስ ዳዊት መልዕክት ላኩ። ዳዊት በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነገሰ መሪ ነው፡፡ 

ክርስቲያኖቹ የላኩት መልዕክት የሚከተለው ነው። 

"ሙስሊሞች ወረውናል። የክርስቶስን ስም እንዳናመሰግን መስቀሉንም እንዳንሳለም አውከውናል። በትህትና የምናቀርበውን ልመናችንን ስምተህ በፍጥነት ደርሰህ አድነን። እንደምታውቀው በእመቤታችን ማርያም ፍቅር ከኢትዩጵያውያን ጋር አንድ ቤተሰብ ነን።"



የንጉስ ዳዊት ልብ ግብጽ ውስጥ በደረሰው የክርስቲያኖች በሙስሊሞች መሳደድ በሃዘን ተነካ። በቁጣ "ክተት ሰራዊት፤ምታ ንጋሪት" አለ።



2.የአባይ መገደብ፥ የዓለም ክርስቲያኖችና የግብጽ መስሊሞች እርቅ፤


ንጉስ ዳዊት ከሸዋ (6) በመነሳት እስከ ሴናር ተጓዘ። ሴናር እንደደረሰም አባይ ወንዝ ወደ ግብጽ እንዳይፈስ ገደበ። ይህን ያደረገው ግብጾች በሃገራቸው ክረምት ስለሌለ እና የአባይ ወንዝ መፍሰስ ከተገታ እህል ዘርቶ ማብቀልም ሆን ማምረት አይችሉም በሚል ነበር። ንጉሱ አባይን ከገደበ በሗላ ለእየሩሳሌም፣ ለሶርያ፣ ለአርመን፣ ለሮማ (ለግሪክ ለማለት ነው) እና ለፈረንጅ ክርስቲያኖች የሚከተለውን መልዕክት ላከ። "ወገኖቼ፤ ደረስኩላችሁ። ለናንተ ስል አባይን ገድቤዋለሁ። ይህን ያደረግሁት ቀድሞ በንግርት ባለው መሰረት ነው። ደግሞ አባይን መገደቤ የመጀመረያ ቅጣት ሲሆን ቀጥዬ ወደ ጠላቶታችሁ ተሻግሬ ሃገራቸውን አጠፋዋለሁ።የሚሆነው ሁሉ በጌታ ፍላጎት ነው።"


ይህ የንጉስ ዳዊት መልዕክት ሲደርሳቸው ክርስቲያኖች እጅግ ተደሰቱ። ለንጉሱ በጻፉት መልስ "አምላክ የኢትዩጵያን ንጉስ ይጠብቅ፤ ዘመቻውንም ይምራ" አሉ። ለንጉሱም ጸሎት ማድረስ ቀጠሉ። "ከጠላቶቻችን ካዳንከን መቶ ሺህ ወቄት ወርቅ ገጸ በረከት እናቀርብልሃለን" የሚል ቃልም ገቡ።

የኢትዩጵያው ንጉስ ከባህር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዞ ዘመተ። ሴናር ሲደርስ የግብጽ ሙስሊሞች ከፍተኛ ፍረሃት አደረባቸው። ልጅ አዋቂው ሳይቀር ከሩቅ ሃገር ጭምር ተሰብስበው መክረው የሚበጃቸውን መላ ካገኙ በሗላ ለእየሩሳሌም ክርስቲያኖች ይህን መልዕክት ላኩ።

"በአምላክ ይዘናችሗል። በሠላም ተውን፤ እኛም እንተዋችሗለን። ካሁን በሗላ ጥቃት ልናደርስባችሁ አንመጣም። የምታመልኩትንም እንዳታመልኩ ችግር አንፈጥርባችሁም። አንጠላችሁም። ሃይማኖታችሁን አናዋርድም። ከአያት ቅድመ አያቶቻችሁ ከወረሳችሁት ሃይማኖች አንለያችሁም። በተራችሁ ከእኛ ጥቃት ሊጠብቃችሁ የመጣው የኢትዩጵያ ንጉስ ከምድረ ገጽ ሳያጠፋን ከእኛ ጋር ዕርቅ አድርጎ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ መልዕክት ላኩበት።"

ይህ መልዕክት የደረሳቸው የዓለም ክርስቲያኖች አምላክን በሙሉ ልብ አመሰገኑ። የገቡትን ቃል በማክበር ለንጉሱ ከመቶ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር እንዲህ ከሚል ከደብዳቤ ጋር ላኩ። "ሰላምታችን ይድረስህ፤ አምላካችን በአንተ አማካይነት ከጠላቶቻችን ጥቃት አድኖናል። እናመስግንሃለን።... አሁን ሙስሊሞችን በሰላም ተዋቸው፤የአባይን ውሃም ልቀቅላቸው።"

ንጉስ ዳዊት ደብዳቤው ሲደርሰው ደስ አለው። ድርጊቱ የእርሱ ሳይሆን የአምላክ ሥራ መሆኑን ገልጾ መልሶ ጻፈላቸው። ቀጠሎም ለግብጽ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች የሚከተለውን መልዕክት በአምባሳደሮቹ አማካይነት ላከላቸው። "እናንት የግብጽ ሙስሊሞች፤ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ዕርቅ ማድረጋችሁ ደግ አድርጋችሗል። ከአሁን በሗላ የዕርቅ ቃል ኪዳናችሁን ሳታፈርሱ በጨዋነት አብራችሁ ኑሩ።"

ይህንኑ ምክር በመስማት ይመስላል የግብጽ ሙስሊሞች የዕርቅ ቃል ኪዳናችውን አክብርው ለብዙ መቶ ዓመታት ክርስቲያኖች ጋር የኖሩት።



3. አባይ፥ የዝናብ መጥፋትና የደማቁ የመስቀል በዓል መወለድ፤


ለሌሎቹን ክርስቲያኖች ደግሞ ይህን ፃፈ። "ከአናንተ የምፈልገው ወርቅና ገንዘብ ሳይሆን ወዳጅነታችሁን ስለሆነ የላካቸሁልኝ ስጦታዎች መልሼ ልኬላችሗለሁ። አምላካችን እኛን የገዛው በደሙ እንጂ በወርቅና በብር አይደለም። እኔ ለክርስቶስ ካለኝ የዕምነት ፅናት የተነሳ በዚህ ረዥም ጉዞ አልደከምኩም፤ ... ይልቁንም ... ለሃገሬ ተስፋ የሚስጥ ነገር አድርጉልኝ፡፡ ሃገሬ በተምች ተመትቷል። ረሃብ ገብቷል፡፡ ዝናብ ጠፍቷል። ጌታችን ተቸንክሮ የሞተበትን ግማደ መስቀል ላኩልኝ፡፡ የተቸገረን የረዳ አንደሚካስ ታውቃላችሁና፡፡"

ፓትርያርኮቹ፣ ቀሳውስቱና ምዕመናኑ የመስቀሉን የቀኝ ግማድ ለንጉስ ዳዊት ላኩለት። ንጉሱ መልሶ የላከላቸውንም ወርቅ በአምላካችን ቤት አኖሩ፡፡ ግማደ መስቀሉ መስከረም 10 ቀን ተተከለ። በዚህ ቀን በመላ ኢትዩጵያ አንፀባራቂ ብርሃን ታየ። የሃገሪቱ ሕዝብም፥ ወንድ ሴት፣ ልጅ አዋቂ ሳይለይ ከንጉሱ ጭምር በደስታ ተሞሉ፥ ክብረ በዓልና ድል ያለ ግብዣ አደርጉ። በዓሉም የአፄ መስቀል በመባል ይጠራ ጀመር። ቀኑ ቀደም ብሎ በንጉስ ዓምደ ጽዩን ጊዜ ይከበር ከነበረው ከቅዱስ መስቀል በዓል ጋር ይገጣጠማል። የቅዱስ መስቀል በዓል በጥንቱ የከፋ ክርስቲያን ዙፋናዊ አገዛዝና በጋሎች (አሁን ኦሮሞዎች) ጭምር ይከበር ነበር። በዓሉ ዛሬ መስቀል በመባል የሚታወቀው ሲሆን በየዓመቱ መስከረም ላይ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።

መስቀሉ ኢትዩጵያ ከደረሰ በኍላ ተምች ወደመ፣ ረሃብ ተወገደ፣ ዝናብ መጥፋት አቆመ። በጎ አድራጎትና ወንድማማችነት ሰፈነ። መስቀሉ ሙታንን በማስነሳትና ታማሚዎችን በመፈወስ ብዙ ተዓምራት ሰራ። በመስቀሉ ሃይል የንጉሱ ጠላት የነበሩ በሙሉ ተገዙለት።




4. የአባይ አቅጣጫ መቀየር ወይም መገደብ ፍራቻ ታሪክ የግብጽና የቱርክ የመከላከል እርምጃዎች እንዲሁም የሕንድ ፍላጎት ፤ 


እቅዱ ከወቅቱ ጋር ሲታይ እንደ ህልም የሚቆጠር ቢሆንም አባይ በኢትዩጵያ ሊገደብ ወይም አቅጣጫው ሊቀየር ይችላል የሚል ፍራቻ በግብጽ ሰፍኖ ኖሯል። አኤች ኤም ጀምስ የሚባል ጸሐፊ፥ "የአባይ ውሃ መጠን ግብጽ ላይ እጅግ ስለቀነሰ የግብጹ ከሊፍ ውሃው የቀነሰበትን እውነተኛ ምክንያት በመጠራጠር ፓትርያርኩን በ1093 ላይ ብዙ ሥጦታ አስይዞ ወደ ኢትዩጵያ ንጉስ እንደላከው በአሌክሳንድርያው ፓትርያርኮች ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል"(7) ብሏል። መልዕከቱ የደረሳቸው የኢትዩጵያ ንጉስና የኃይማኖት መሪዎች ፀሎት ካደረሱ በሗላ በአንድ ምሽት አባይ ሦሥት ክንድ ከፍታ ጨምሮ እንዳደረ ጽፏል። 

አኤች ኤም ጀምስ በመቀጠል በዛጉኤ ሥርወ መንግሰት በተለይ በአስራ ሦሥተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሸ ከነገሱት ንጉሶች ከመጨረሻዎቹ አንዱ የኢ- አማንያን (Infidels) ሃገር ብሎ የጠራትን ግብጽን ሙሉ በሙሉ በርሃ ለማድረግ የአባይን የፍሰት አቅጣጫ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ለማዞር ሥራ የጀመረ ቢሆንም ሥራው ሳይጠናቀቅ ቀረ ይላል። ጀምስ ይህ የሆነው አንዳንዶች ንጉሱ ስለሞተ ነው ሲሉ የተቀሩት ደግሞ የንጉሱ አማካሪዎች ግብጽን በረሃ ማድረግ ከፈለገ አባይን በተመሳሳይ ሁኔታ ኢ - አማኒ ወደሆነችው ሶማልያ እንዲፈስ በማድረግ በረሃ የሆነውን ሃግራቸውን እንደሚያለማላቸውና ሃብታምና ጠንካራ የሆነ ጠላት ለኢትዩጵያ እንደሚተው ስላስጠነቀቁት ነው ሲል ደመድሟል።


በ 1325 ደግሞ ንጉስ አምደ ጽዩን ግብጽን በርሃ አደርጋታለሁ በሚል ገዢዋን ሱልጣን ኢን ናዚርን በማስፈራራት ኮፕቶችን ከመሳድድ አድኗል። ይህ ከላይ ከቀረበው ከቀዳማዊ ዳዊት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል።


የኢትዩጵያ ንጉስ አባይን በመገደብ ወይም አቅጣጫ በመቀየር ግብጽን የማስራብም ሆነ የማጥፋት መላ እንዳለው በሰፊው እየታመበት የመጣው በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።(8) ሉዶልፍ ነገሩ በሰፊው የታመነበት ለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ቱርኮች ኢትዩጵያ አባይን ትገድብ ወይም አቅጣጫ ትቀይር ይሆናል በሚል ፍራቻ እንዳትሞክረው ማካካሻ ክፍያ ማድረጋቸው ነው ይላል። ብሩስ አባይን የመገደብ ወይም አቅጣጫ የመቀየር እቅድ በንጉስ ላሊበላ ዘመን ብዙ ታስቦበት በሗላ እንደተተወ ጽፏል።(9) ባሰት ደግሞ እቅዱ በድጋሚ በንጉስ አምደ ጽዩን ዘመን ተነስቶ ነበር ይላል።(10) በአስራ ስድስተኛ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የሕንድ ምከትል ንጉስ የነበረውን አልቡከርክ የኢትዩጵያ ንጉስ አሳምኖ አባይን በማድረቅ ግብጽን በረሃ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበረው ተጽፏል።(11) የሕንዱ ንጉስ ፍላጎት በቬኒስ ቁጥጥር ስር ወድቋል ያለውን የሃገሩን ንግድ ለማላቀቅና በፓርቹጋል እጅ በነበረው በደቡብ አፍሪካ ጫፍ በኩል ንግዱን ማካሄድ ስለፈለገ ነበር።


5. የግብጽ ያልተሳኩ የጦርነት ትንኮሳዎች፤





ከታሪካቸው መጀመሪያ እስከ አሁን ሥልጣኔያቸውን፤ ብልጽግናቸውንና መላ ሕይወታቸውን በአባይ ወንዝ ላይ የገነቡት ግብጾች ለኢትዩጵያ ንጉሶች አማላጆችና ስጦታዎች መላክ እንዲሁም ትዕዛዞቻቸውን መፈጸም ሲያንገሸግሻቸው መውጫ መንገድ ፈለጉ።የግራኝ መሐመድ ወረራና የኦሮሞዎችን መስፋፋት ተከተሎ የመጣው የዘመነ መሳፍንት ጦርነት ኢትዩጵያን እንዳዳከማት ካዩ በሗላ ሃገሪቱን በሃይል በመያዝ የአባይን ያልተገታ ወደ ግብ ጽ ፍሰት ማረጋገጥ ፈለጉ።


ጊዜው የኦቶማን (ቱርከ) ኢምፓየር እየደከመ ግብጽ ደግሞ ጠንካራና ሃይለኛ እየሆነች የመጣችበት ሲሆን ፍላጎቱ ወሰን የሌለው አዲሱ ከህዲፍሱዳንንና ኢትዩጵያን ጠቅልሎ ለመያዝ ፈለገ። ይህ የሆነው ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ሲሆን ወደ ኢትዩጵያ የዘመቱትም በዚህ ጊዜ ነበር። ነገር ግን አልቀናቸውም። በመጀመሪያ ጉንደት ላይ በ1874 እንዲሁም ላይ በ 1876 ከኢትዩጵያ ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ተሸነፉ።ጉንደትና ጉራዕ ዛሬ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም ሁለቱንም አልፈው ወደ መሃል ሃገር ዘልቀው እንደነበር ይታወቃል። በጦርነቶቹ በቅጡ ስለተደቆሱ ኢትዩጵያን በቀጥታ በሃይል የመያዝ ህልማቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል። በተዘዋዋሪ ጥቃት ከማድረስ ግን አላቆሙም። 



6. ታላቍ ብሪታንያ፤ የወደፊቱ የአባይ ሁነታ ገብቷት የነበረች ሃገር፤



የአባይ በመገደብ ወይም አቅጣጫ በመቀየር ሥልጣኔም ጉልበትም አላቸው ከተባሉት ቅኝ ገዢዎች መካከል አውራ የምትባለውን እንግሊዝ ሳይቀር ያሳሰበ ጉዳይ ነበረ። ከዚህም የተነሳ በኢትዩጵያና በእንግሊዝ መካከል ጥር 16/ 1902 ስምምነት ተፈረመ። የስምምነቱ አንቅጽ 3 እንደሚከተለው ይነበባል። 

“የኢትዩጵያ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ምንሊክ ከብሪታንያ መንግሰትና ከሱዳን መንግስት ጋር መግባባት ላይ ሳይደረስ በአባይ ወንዝ ላይ እንዲሁም በጣና ሃይቅ ላይ ወይም ሶባት ወደ አባይ በሚያደርግው ፍሰት ላይ ግንባታ ላለማካድ ወይም ለግንባታ ፍቃድ ላለመስጠት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ተስማምተዋል”(12)

ዛሬ ግብጽ ይህ የስምምነት አንቀጽ ከእኔ ጋር መግባባት ሳይደረስ በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይካሄድ ለማነሳው ክርክር ይደግፈኛል ትላለች። የቀድሞው ቅኝ ገዥ የብሪታንያ መንግስት ወራሽ ስለሆንኩ ያ መንግስት ከኢትዩጵያ ጋር ያደረገው ስምምነትም ወራሽና ተጠቃሚ ነኝ ባይ ናት። የኢትዩጵያ መንግስት ይህን ክርክር አይቀበልም። 




ማጠቃለያ


ከላይ እንደቀረበው አባይ ኢትዩጵያንና ግብጽን በየተራ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች እንዲሁም ተፎካካሪ ሲያደርጋቸው እስከ አሁን ዘልቋል። ከአሁን በሗላ ሁኔታው በበላይና የበታች እንዲሁም ተፎካካሪነት ሊካሄድ የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ድሮ ስልጣኔ እንዳሁን ባለተስፋፋበት እና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልዳበረበት ወቅት የተፈጠሩ የስነልቦና ውጥረቶችና ፍራቻዎች ወደ ጦርነት እንዲለወጡ መፍቀድ ስህተት ነው። ዘመኑ ስለተለወጠ ኢትዩጵያ እንደጥንቱ ግብጽን ልታሽቆጠቁጣት አትችልም፤ አይገባትምም። ግብጽም በሃይል ተመክታ የኢትዩጵያን ልማት ልታሰናክል አይገባትም። በአሁን ወቅት የሚታየው አለመተማመንና መፍትሄ መጠፋት ከፊል ምክንያቶች ለዘመናት የቆዩ ውጥረቶችና ፍራቻዎች አካል ሲሆኑ ለመተማመን መንገድ እንዲለቁ ጥረት ማደረግ ያስፈልጋል። እስካሁን አባይ ለግብጽ ብቻ ነው። ለወደፊት የሁለታችንም መሆን አለበት። ኢትዩጵያውያን ሁላችን በአንድ ሆነን በዚህ አቅጣጫ ብንሄድ ይበጀናል።


__________________________________


(1) ከ1850 እሰከ1855 ባሉት ዓመታት ከጉራጌ እናትና ከኦሮሞ አባት የተወለዱት ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ ትምህርታቸውን ሸዋ ውስጥ ከነበሩት ሁለት ወይም ሶስት የባህል ማዕከሎች አንዱ በሆነው አንኮበር ፈጽመው የመጀመሪያዋ የአፄ ምንልክ ሚስት የወይዘሮ ባፈና ፀሐፊ ሆኑ። አፄ ምንሊክ በ 1877 ወደ ጎንደርን ለማቅናት ሲሃዱ አብረው ሂዱ። በ 1880 የቢተመንግስት ታሪክ ፀሐፊነት ሃላፊነት ተሰጣቸው። አከታትሎም ፀሐፊ ትእዛዝነት እና የእንጦጦ ራጉኢል ቢተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ተጨመረላቸው። በ 1908 በጽሕፈት ሚኒስትርነት ተሹመው በማገልገል ላይ እያሉ በ1912 አረፉ። 

(2) ከኢትዩጵያ የሚነሳው አባይ አቍዋርጦ ከሚያልፋችው የአንግሎ - ግብጽ ሱዳን ክፍለ ሃገራት አንዱ ሴናር ሲሆን በዚሁ ሥም የሚጠራ ከአባይ ቀኝ መዳረሻ ላይ የሚገኝ ከተማ ም ነበር። “የሴናር ንጉስ በከፊል በኢትዩጵያው ንጉስ አስተዳደራዊ ጥበቃ ስር ስለነበር የንጉሱ የሆነ ነገር ሁሉ ክፍለ ሃገሩን አቅዋርጦ የሚያልፈው ያለ ምንም ክፍያ ነበር። (Memoire de M. du Maillet, consul general de France en Egypte en date du 12 mai 1698, cite par De Caix de Saint- Aymour, Hist. Des relations de la France avec l’Abyssinie chretienne, p. 219, n.2).

(3) እንደ ሙስሊም ታሪከ ጸሃፊዎች ከሆነ ይህ ክርስቲያኖችን በሃይል የማሳደድ ድርጊት የተጀመረው ከ 1352 ነው።

(4)የኮንስታቲኖፕልእዚሀ መጨመር ስህተት ይመስላል። ምክንያቱም ቀዳማዊ ዳዊት ንጉስየነበረው ከ1380 አስከ 1409 ሲሆን ኮንስታቲኖፕል በሙስሊሞች አጅ የወደቀው በ1453 ስለሆነ ነው። 

(5) በስህተት ሮማ የተባለው ግሪክ ለማለት ነው።

(6) በወቅቱ ሸዋ ኢትዩጵያ ውስጥ ከነበሩ ስርወ መንግስታት አንዱ ነበር። አጅግ ጥንታዊ በሆኑ የኢትዩጵያ ካርታዎች ላይ እንደሚታየው በምዕራብ ከአባይ ወንዝ፤ በደቡብ ምዕራብ የአባይ መጋቢ ከሆነው ሙገር ወንዝ፤ በደቡብ ከአዋሽ ወንዝ፤በምስራቅ ከአንኮበር የተራራ ሰንሰልቶች፤ በሰሚን ከአዳባይ ጋር ይገናኛል። በንጉስ ሳህለ ስላሰ ዘመን ከምዕራብ በስተቀር በሰሜን መንዝን፤ በምስራቅ ይፋትን አና በደቡብ ምንጃርን በማጠቃለል በየአቅጣጫው አደገ።(KRAPF, Reisen..., t. I, p. 62) 

(7) A.H.M. Jones, ''Historie de l'Abyssinie des origine à nos jours'' (1935)

(8) Perruchon, Vie de Lalibala, p. XXIII, note 2. Cf. D. De Rivoyre, Aux pays du Soudan, p. 236) Lud olf, Nouv. Hist. d’Abissini, ed. de 1684, p. 28.

(9) Bruce, t. I, pp. 609 - 611

(10) Basset, Etudes ... , p.233.

(11) Le Grand, dans Lobo, Voyage hist. d’Abissinie, pp. 215-219.
(12) Trad. Donne e par Pierre - Alype dans L’Ethiopie et les convoitises allemandes, p. 154.

GLOBAL CONFLICT AND DISORDER PATTERNS: 2020

This paper was presented at the 2020 Munich Security Conference at a side event hosted by the Armed Conflict Location & Event D...