Tuesday, September 29, 2015

ኤርትራ - ለራሷ ያልሆነች ሃገር፣ የኢትዩጵያ ፈተና


                                                                              By EF Staff Writer



Image result for ethiopia and Eritrea
የኢትዩጵያና የኤርትራ  መንግስታት ዋና ችግር በሁለቱ ሃገሮች መካከል የተካሄደው የሁለት ዓመት ጦርነት 2000 ላይ ሲያበቃ ይህንኑ ተከትሎ አልጀርስ ላይ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሰጠው ውሳኔ አፈጻጸም እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። 

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ሁለት ጥያቄዎችን ለመ
ለስ ነው:: ንደኛው፥ "የኢትዩጵያና የኤርትራ መንግስታት ችግር የድንበሩ ውሳኔ አፈጻጸም ወይስ በቅን ልቦና ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት ማጣት?" የሚለው ሲሆን ሌላው፥ "ፍላጎቱን ያጣው አንዱ ወይስ ሁለቱም ናቸው?" የሚለው ነው።

ለመነሻ ያህል - የካሳ ኮሚሽን ውሳኔ፥


አሁን ወደመዘንጋት የተቃረበ ቢሆንም በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የካሳ ኮሚሽንም ተቋቋሞ ነበር። ኮሚሽኑ ሁለቱ መንግስታት ከግንቦት 1998 እስከ ሰኔ 2000 ባካሄዱት ጦርነት አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱትን ጉዳት በመለየት አንዳቸው ለሌላው ሊከፍል ይገባል ያለውን የካሣ መጠን በመወሰን ሥራውን ነሓሴ 17/ 2009 አጠናቋል።

በሁለቱ ዓመት ጦርነት ከፍታኛ የህይወት፥ የአካልና የንብረት ጉዳት እንዲሁም ዘረፋ፥ የህዝቦች መፈናቀልና መብቶች መጣስ ደርሷል።ይህም ሆኖ ኮሚሽኑ የኤርትራ መንግስት ሊከፈለኝ ይገባል ካለው 6 ቢሊዩን ዶላር ውስጥ እጅግ ከፍታኛውን እጅ ውድቅ በማድረግ 163 ሚሊዩን ዶላር በኢትዩጵያ መንግስት እንዲከፈለው የኢትዩጵያ መንግስት ደግሞ ሊከፈለኝ ይገባል ካለው 14.3 ቢሊዩን ዶላር ውስጥ እንዲሁ እጅግ ከፍታኛውን እጅ ውድቅ በማድረግ 174 ሚሊዩን ዶላር በኤርትራ መንግስት እንዲከፈለው ወስኗል። አንዱ መንግስት ለሌላው እንዲከፍል የተወሰነው ዕዳ ቢቻቻል የኢትዩጵያ መንግስት ከኤርትራ መንግስት ላይ 10 ሚሊዩን ዶላር ይፈልጋል።ኢትዩጵያን የወከሉ ጠበቆች ድክመት ለተወሰነው አነስታኛ ካሳ አስተዋጸኦ አድርጓል ያሉ ጥቂት አይደሉም።

የካሣው ውሳኔ እንደታወቀ የኤርትራ መንግስት ውሳኔውን እንደተቀበለ አስታውቋል። አንዳንድ ጥናቶች የኤርትራ መንግስት በውሳኔው ተጠቅሟል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። ይህንንም ሲያስረዱ የሚሰጡት ምክንያት ከኢትዩጵያ እንዲወጡ የተደረጉ ኤርትራውያንን በሚመለከት ኮሚሽኑ ለኤርትራ መንግስት 43 ሚሊዩን ዶላር ካሳ እንዲከፈል ያዘዘ ሲሆን የኢትዩጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰዎቹ ወደ ኢትዩጵያ በመመልስ ንብረታቸውን፤ ንብረቱ ከተሸጠም ዋጋውን መውሰድ እንደሚችሉ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ በማድረጉ ለአንድ ጉዳት ሁለቴ ተከፍሏል በሚል ነው።በዚህ ላይ በጦርነቱ ወቅት አሰብና ምጽዋ ላይ የነበረ ዋጋው 117 ሚሊዩን ዶላር የሆነ በኤርትራ የተወሰደ የኢትየጵያውያን ንብረት በካሳ አለመያዙን ያክላሉ። ሁለቱ ተደማምረው ከኤርትራ መንግስትላይ የሚፈለገውን 10 ሚሊዩን ዶላር ወደ 170 ሚሊዩን ያስጠጋው ነበር ባይ ናቸው።

የኢትዩጵያ መንግስት ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ ባሳለፈው ውሳኔ ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ን እንደጣሰችና ኢትዩጵያን እንደወረረች ማረጋገጡን አስታውሶ ለኢትዩጵያ እንዲከፈል የታዘዘው ገንዘብ ከደረሰው ጉዳት ጋር ሲመዛዘን አነስተኛ መሆኑን ገልጿል። አያይዞም ውሳኔውን እንደሚያጠናው አመልክቶ ኤርትራ ለኢትዩጵያ መክፈል ያለባትን ክፍያ የምትፍፈጽምበትን ሁኔታ እንደሚከታተል አስታውቋል።

ኢትዩጵያ መንግስትና በኤርትራ መንግስት መካከል በሶስተኛ ወገን አማካይነትም ሆነ በቀጥታ የንግግር መስመር ባለመኖሩ መንግስት በካሳው ጉዳይ የሚከታተለው ነገር ላይኖር ይችላል። ይህን ሆኖ ክትትል ተደረጎ ውጤቱ ስለመገኘቱ የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ እንዳልተሞከረ መገመት ይቻላል።



የድንበሩ ጉዳይ አሁን ያለበት የህግ ሁኔታ፥


ከ 2002 ቱ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በኋላ የማካለል (delimitation) ስራ በኮሚሽኑ የተካሄደ ቢሆንም ቀሪው የምሰሶ ማቆሙ ሥራ (demarcation) የኢትዩጵያ መንግስት የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ (human and physical geography) ግምት ውስጥ ገብቶ “ሰጥቶ በመቀበል” ማስተካከል ካልተደረገ ምሰሶ አይቆምም በማለቱ ተቋርጧል።

የኤርትራ መንግስት ደግሞ በኢትዩጵያ መንግስት የቀረበው “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ” ጉዳይ የኮሚሽኑን ውሳኔ ማስተካከል ስለሆነ አልቀበለውም፥ ውሳኔው እንዳለ ይፈጻም በማለት ተቃወሟል።

የድንበር ኮሚሽኑ ለሁለቱም መንግስታት በቂ ግዜ ስጥቶ በተለያዩበት ጉዳይ ይስማሙ እንደሆነ ቢጠብቅም መፍትሄ ባለመታየቱ ከኅዳር 30/ 2007 ጀምሮ ድንበሩን በአገናኞች (coordinates) አማካይነት ለይቶ (demarcate አድርጎ) በሁለቱ ሃገሮች መካከል ምሰሶ ማቆም ከሚኖረው አስገዳጅነት ያላነሰ ውጤት አለው ያለውን (virtual boundary) ድንበር አቁሞ ስራውን ፈጽሟል።

የኢትዩጵያ መንግስት በበኩሉ ኮሚሽኑ ድንበሩን በአገናኞች (coordinates) መለየቱ ምሰሶ ማቆም ከሚኖረው አስገዳጅነት እኩል ውጤት የለውም በሚል ድርጊቱን ውድቅ ማድረጉን አስታወቀ።

የኤርትራ መንግስት በመጀመሪያ ጉዳዩ በአካል ምሰሶ በማቆም መጠናቀቅ አለበት በማለት የድንበሩን በአገናኞች መለየት(virtual boundary) ለመቀበል ቢያንገራግርም ትንሽ ዘግይቶ ነገርየው ወደሚፈልገው የመጨረሻ ግብ ይበልጥ እንደሚያስጠጋው በመረዳት ተቀብሎታል።


"የሰላም እቅድ"


የኢትዩጵያ መንግስት የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ (human and physical geography) ግምት ውስጥ ገብቶ “ሰጥቶ በመቀበል” ማስተካከል ካልተደረገ ምሰሶ አይቆምም ያለውን የኤርትራ መንግስት ውድቅ እንዳደረገ እንዲሁም በአገናኞች የተለየውን ድንበር መቀበሉን ከተረዳ በኋላ ይመስላል 2009 ላይ " ባለ አምስት ነጥብ የሰላም እቅድ" አወጣ።

የሰላም እቅዱ "የኢትዩጵያ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ "በመሰረቱ" መቀበሉን፣ የድንበሩ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንዳለበት፣ በሁለቱን ሃገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ስርዓት ለማስያዝ በመነጋገር የግጭቱን መሰረታዊ ምክንያቶች መፍታት ፥ ዘላቂ ሰላምን በሚያሰፍን እና የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነትና መተሳሰር በሚያጠናክር መልኩ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ባስቸኳይ ንግግር መጀመር " እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ ነው።

ከላይ እንደሚነበበው “የሰላም እቅዱ” ስለ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ (human and physical geography) ግምት ውስጥ ገብቶ “ሰጥቶ በመቀበል” የድንበሩን ችገር መፍታት አይናገርም። “የሰላም እቅዱ” በኋላ የወጣ ስለሆነና ስለ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ - - -” ስለማይናገር በዝምታ ሽሮታል የሚሉ ተንታኞች አሉ። ሃሳባችው ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር የሚታየው “በሰላም እቅዱ” ብቻ ስለሆነ ከኤርትራ ጋር መነጋገር የሚያስፈልገው ስለዘላቂ ሰላም ብቻ ይሆናል የሚል ነው።

ለዚህም እንደ ማሰርጃ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኢትዩጵያ መንግስት ባልስልጣኖች ሲናገሩ የሚያነሱት “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ - - -” ጉዳይ ትተው የሰላምን ነገር ብቻ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አያይዘውም ይህ ከሆነ ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ ይችላል በሚል ይደመድማሉ። የዚህ ተቃራኒ ትንታኔ የሚሰጡ ደግሞ የህግ አተረጓጎም ዘዴ በመጠቀም “የሰላም እቅዱ” በግልጽ ባይናገርም “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ - - -” ጉዳይ በውስጡ ይዟል ይላሉ። መደምደሚያቸው ሁለቱ ሰነዶች አብረው የሚታዩ በመሆናቸው አንዳንዶች እንደሚያስቡት ችግሩ ቀላል አለመሆኑን ያሰምሩበታል።

ለማንኛውም በዚህ ነጥብ ላይ በግዜ ብዛት የፖሊሲ ግልጽነት ችግር የሚታይ ይመስላል። ይህም ሆኖ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ - - -” ጉዳይ ቀርቷል ቢባል እንኳ የኤርትራ መንግስት በሰላም እቅዱም ላይ ለመነጋገር ፍላጎት የለውም።


የአቋሞቹ ህጋዊነትና ትክክለኛነት፥


የህግ አስገዳጅነት ያለው የግልግል ስምምነት ከፈረሙ በኋላ የግልግሉ አካል የሰጠውን ውሳኔ መፈጸም ስምምነቱም የዓለም አቀፍ ህግም ያስገደዳሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ የኤርትራ አቋም የሚወቀስበት ህጋዊ ምክንያት የለም። በኤርትራ በኩል መለሳለስ ተደርጎ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ - - -” ግምት ውስጥ ገብቶ ሰጥተን እንቀበላለን ካላሉ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የማታ ማታ የተወሰነላቸውን ማግኘታቸው አይቀርም ብሎ ማሰብ ትክክል ይሆናል። በተግባር ግን የመጨረሻው ውጤት ያ እንደሚሆንና መቼ እንደሚሳካ መናገር አይቻልም። በተለይ በቅርቡ የኤርትራ መንግስት በኢትዩጵያ ላይ በእጅ አዙር የጫረው ጦርነት ግምት ውስጥ ሲገባ ማለት ነው።

የኢትዩጵያ መንግስት ውሳኔውን “በመሰረቱ” መቀበሉ የኤርትራ መንግስት ውሳኔው እንዳለ ይፈጸም በማለት የሚያደርገውን ግፊት ምክንያታዊነትና አስፈላጊነት ጥያቄ ላይ አስቀምጦታል። በወረቀት ላይ የሚደረግ የድንበር ማካለል (delimitation) ከምሰሶ ማቆሙ ሥራ (demarcation) በተወሰኑ ገጽታዋች የሚለይ በመሆኑ የኋላኛው የሚፈጥራቸው ችግሮች ካሉ እንዲታዩ ጥያቄ ከቀረበ መነጋገር የማይቀር ነገር ነው። ንግግሩ እንዲደረግ መጠየቅም ውሳኔውን እንደመሻር ህገወጥነት ተግባር ተደርጎ የሚታይ ድርጊት አይደለም።

የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥን (human and physical geography) አለመመልከት አንድነት የሚሰማቸውን ህዝቦች ለመከፋፈልና ከተሞችና መንደሮች ከመንግስት አስተዳደር ተቋሞችና ከአገልግሎቾች (የፖሊስ፣ የትምህርት፣ የጤና ተቋሞች ወዘተ) መራቅ እንዲሁም ቅሬታ የሚሰማው ህዝብ መፍጠርና ለኋላ ችግር ማቆየት ሊያስከትል ይችላል። ጉዳዩ ዞሮ ዞሮ የሰላምና የጦርነት ጉዳይ ይሆናል። የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ ግምት ውስጥ ይግባ ሲባልም እንዲያው በቅሚያ አይነት የሚፈጸም ሳይሆን “ሰጥቶ በመቀበል” ማስተካከል በማድረግ መሆኑም ተገልጿል።

የኤርትራ መንግስት ለመነጋገር ፈቃደኛ ስላልሆነ የኢትዩጵያ መንግስት የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ የሚላቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ፥ ማንን ይጥቀሙ ወይም ማንን ይጉዱ አያውቅም። በተመሳሳይ ሁኔታ ማስተካከል ለማድረግ ምን ተሰጥቶ ምን እንደሚቀበል አያውቅም። በተመሳሳይ ሁኔታ “የሰላም እቅዱ”ን ውድቅ ከማድረጉ በስተቀር ይዘቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት ፍላጎት አላሳየም። ህዝብ፣ ከተማና መንደር ተከፈለ አልተከፈለ፥ ህዝብ ከአገለግሎት ራቀ አልራቀ አያገባኝም፥ ዘላቂ ሰላም መጣ አልመጣ አይጨንቀኝም። ስለሆነም ቃል ሳይተነፈስ በወረቀት ላይ በተሰመረው መሰረት ምሰሶ ይቁም ባይ ነው።

ከላይ እንደታየው የኤርትራም የኢትዩጵያም አቋም ከህግ አንጻር ሲታይ ስህተት አይታይበትም። የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ልምድና አሰራር ከታየ የኤርትራ መንግስት እንደሚጠይቀው የድንበሩ ኮሚሽን ውሳኔ እንዳለ መፈጸም ድጋፍ አለው። በዓለ ም ዓቀፍ ደረጃም ቢሆን የህግ መከበርና በህግ መሰረት የተሰጠ ውሳኔ በውሳኔው መሰረት መፈጸም ለሃገሮች ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ነው። ውሳኔው እንዳይፈጸም መሰናክል ማቆም እንደበህግ አልገዛም ባይነት ሊቆጠር ይችላል።

ይህም ሆኖ የህግ መኖርና በህግ መሰረት የተሰጠ ውሳኔ ጉዳዩችን ለመቁርጥ የሚረዳ ቢሆንም ሁሌም የሃገሮችን ሰላምና መረጋጋት ያስገኛል ማለት እንዳልሆነዓለ ም ዓቀፉ ማህበረስብ አይስተውም ። ውሳኔው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አያመጣም የሚል በግልጽ የሚታይና አሳማኝ ስጋት ካለ ስጋቱን አለመመልከት ስህተት መሆኑን ይረዳል። በኤርትራና ኢትዩጵያ የድንበር መለየት ጉዳይ ያጋጠመው ይህ ያልተለመደ ውሳኔን ተከትሎ ሊመጣ የሚችል የሰላም መታወክ ችግር መሆኑንም የተገነዘበ ይመስላል። የኤርትራ መንግስትን ጥያቄ በመደገፍ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ እንዳለ ይፈጸም ከማለት ይልቅ የኢትዩጵያን መንግስት የሰላም ፍለጋ መስመር የተቀበለው በዚህ ምክንያት መሆኑን መገመት ይቻላል።

በዚህ ሁኔታ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የኢትዩጵያን መንግስት ሰላም ፍለጋ ለማውገዝ፥ ውድቅ ለምድረግም ሆነ ጥያቄውን መነሻ በማድረግ እቀባ ለመጣል ይቸግረዋል። በተቃራኒው የኤርትራ መንግስት ውሳኔው እንዳለ ይፈጸም ጥያቄ ድጋፍ ማጣት ብቻ ሳይሆን ችግሩን በመነጋገር እንዲፈታ ግፊት ሊደግርበት ይችላል።

    

የሃቻ አምናው ንግግር፥


በድንበሩ ጉዳይ የመጨረሻው ግልጽና ቀጥታ የኤርትራና የኢትዩጵያ መንግስታት የቃላት ልውውጥ የሆነው ሃቻ  አምና በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ ወቅት ነው።

እንደተለመደው የኤርትራ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑ የሰጠው ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈጸም፣ ድንበሩም በውሳኔው መሰረት እንዲከለል የኢትዩጵያ ወታደሮችም ከያዙት የኤርትራ ግዛት እንዲለቁ ህብረቱ እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል።

የኢትዩጵያ መንግስት በበኩሉ የዓለም ዓቀፍ ህግን እንደሚያከብር ውሳኔውም በውይይትና በድርድር ለመጨረስ ዝግጁ መሆኑን አስረድቶ ኤርትራን የአካባቢውን ሰላም በማወክ ይከሳል። ለዚህም እንደማስረጃ በኤርትራ ላይ የተላለፉ የአፍሪካ ህብረት ውሳኔና የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እቀባዎች እንዳሉ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

ይህ የቃላት ልውውጥ የሆነው ስብሰባው በዝግ ሲካሄድ እንደነበረና የተደረገውም ውይይት መጠነኛ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የወቅቱ የጉባዔው ፕሬዚዳንት የሆኑት ሮበርት ሙጓቤ ሃገሮቹ ችግራቸውን በመነጋገር እንዲፈቱ ያቀረቡት ሃሳብ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ድጋፍ ካገኘ በኋላ አጀንዳው እንደተዘጋ ተዘግቧል። በዚህም ጉባዔው የኢትዩጵያን የሰላም ፍለጋ አቋም እንደደገፈ ማንጸባረቁ እንደሆነ ተነግሯል።

የአፍሪካ ህብረት የኢትዩጵያን አቋም መደገፉ የሚያበረታታ ሲሆን የተባበሩት መንግስታትና የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ውጭ ይሄዳሉ የሚል ግምት የለም።


የአቋሞች መራራቅ - ለምን?


ከእነዚህ የተራራቁ አቋሞች በፍጥነት ለመውጣት የሚቻለው የኤርትራ መንግስት ወይም የኢትዩጵያ መንግስት የአቋም ለውጥ ካደርጉ ወይም መለሳለስ ካሳዩ ነው።



መሰናክል - የኤርትራ መንግስት?


የኤርትራ መንግስት የአቋም ለውጥ አድርጎ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ (human and physical geography) ግምት ውስጥ ገብቶ “ሰጥቶ በመቀበል” ማስተካከል አደርጋለሁ ካለና ስለሰላም ለመነጋገር ከተስማማ ችግሩ ተፈታ ማለት ነው።

የቅን ልቦና መጉደለ ካልሆነ በስተቀር ይህን በማደርግ በኤርትራ ላይ የሚደርስ ጉዳት የለም የሚሉ የሁለቱም ሃገሮች ዜጎች አሉ። በተቃራኒው ይህን ባላማድረግ ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ በኤርትራ ህዝብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እንደሚከተለው ይገልጻሉ።
“ብዙ ዓመታት ከባከኑ በኋላ ችግሩን በመነጋገር እንድንፈታ እንገደዳለን። እስከዚያ ድረስ ድንበር አካባቢ ለሰፈሩት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ደሞዝ፤ አበልና ለሚይዙት መሳሪያ ከፍተኛ ወጪ እናደርጋለን። ብሄራዊ ውትድርናን በማስቀጠል ወጣቱን ከትምህርትና ከምርት ስራ እናርቃለን። ጊዜ ሳናጠፋ ወደብ ለኢትዩጵያ በማከራየት ለሃገራችን ልማት የሚሆን ከፍተኝ የኪራይ ገቢ ማግኘት አንችልም። በድንበር አካባቢ በንግድ መጠቀም አንችልም። ድንገት የተቋረጠውን የታሪክ፤ የባህልና የሶሻል ግንኙነቶች መጠገን አይታሰብም። የትም ለማይደርሱ ግንቦት 7 ፥ አርበኞች ግንባርና ኢሳት ገንዘብ እናባክናለን። በዚያውም ሃገራችንን ሰላም ወደማጣትና አለመረጋጋት አልፎ ተርፎም ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ እንፈጥራለን። ዘላቂ ጠላት በማበራከት ሃገራችንን የከፋ ችግር ላይ እንጥላለን።”
እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ የኤርትራ መንግስት ስለሰላም ለመነጋገር በመወሰን ብቻ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ይህ ባለመሆኑ የኤርትራ መንግስትን ለህዝቡ ያልሆነ ህዝቡን ደግም በመንግስት ላይ ጫና ስለማያደርግ ለሃገሩ ያልሆነ ይሉታል።

ታደያ የኤርትራ መንግስት ይህን ከማድረግ ያገደው ነገር ምንድነው? እንደሚመስለን ከሆነ በመጨረሻው ጦርነት ያጣውን ወታደራዊ ድል በህግ አሸናፊነት የመውጣት ፍላጎት ነው። የድንበሩም ሆነ የካሳው ኮሚሽን ውሳኔዎች በጦርነቱ አሸናፊውም ሆነ ተሸናፊው ማን እንደሆነ አያሳዩም። ኮሚሽኖቹ የዚህ ዓይነት ትንታኔ ውስጥ አይገቡም፥ አልገቡምም። ሁለቱም መንግስታት አንዳቸው ሌላውን እንዳሸነፉ ለህዝባቸው ቢናገሩም በጦርነት ሁለት አሸናፊ ሊኖር ስለማይችል የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ባይናገርም የኢትዩጵያ የበላይነት አመላክቷል።

ትዝ እንደሚለን በወቅቱ ጦርነቱ ያበቃው የኢትዩጵያ መንግስት አወዛጋቢ የሆኑትን ቦታዎች በሙሉ ከያዘና የኤርትራ መንግስትም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ/አ/ድ) ዕቅድ መሰረት ጦርነቱ ሲጀመር ወደነበረበት ቦታ እንደሚመለስ ካረጋገጠ በኋላ ነበር። ይህን ማድረግ እጅግ ኩሩ የሆነው የኤርትራ መንግስት እንደሞት የቆጠረው ጉዳይ ሲሆን የአፍሪካ ህብረትንም ሆነ የኢትዩጵያ መንግስት በተራቸው ማሳፈር የሚቻለው የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ እንዳለ ሲፈጸም፥ የኢትዩጵያ ወታደሮች የያዙትን የኤርትራ መሬት ለቀው ሲወጡ ፥ የኤርትራ ባንዲራ ሲውለበለብና ወታደሮቿ በባንዲራው ስር ሲጨፍሩ ነው። ይህ ደግሞ እስካሁን አልሆነም።


ያም ሆነ ይህ የኢትዩጵያ መንግስት ባድመን ቢያስረክብም  ፕሬዚዳንቱ በኢትዩጵያ የመንግስት ለውጥና ሀገመንግስቱንና የፌደራላዊ አደረጃጀቷን እሳቸው  በሚፈልጉት ዓይነት የመተካት ጥያቄ ችግር መፍጠሩ አይቀርም::


መሰናክል - የኢትዩጵያ መንግስት?


የኤርትራ ጥያቄ ተቀባይነት ባያገኝም የኢትዩጵያ መንግስት መነጋገር ሳያስፈልገው ውሳኔውን እንዳለ ለመፈጸም ዝግጁነቱን ከገለጸ ችግሩ ተፈታ ማለት ነው።

በኤርትራው ጉዳይ እንደሆነው ሁሉ የኢትዩጵያ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ “በመሰረቱ” ተቀብያለሁ ካለ በኋላ “የሰዎች አሰፋፈርና የመሬት አቀማመጥ ግምት ውስጥ ገብቶ “ሰጥቶ በመቀበል” እንፍታው እንዲሁም ስለዘላቂ ሰላም እንነጋገር ያለው በክፉ ልቦና እንደሆነ የሚገምቱ ሰዎች አሉ።

ሰዎቹ ግምታቸውን ሲያብራሩ ፦
"አወዛጋቢ የተባለው ድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦች ከሁለቱ አንዱን ሀገር መርጠው ወደፈለጉት ሊሄዱ እንደሚችሉ፥ ምናልባትም በአሁን ወቅት አንደሄዱ፥ከተማና መንደሮች የተባሉትም ይህ ነው የሚባል የታሪክም ሆነ የኢኮኖሚ ፋይዳ እንደሌላቸው፥ የመሬት አቀማመጥም ቢሆን የተፈጥሮ ነገር ስለሆነ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ይናገራሉ። የዘላቂ ሰላም ጉዳይም ቢሆን የክልሉ ወታደራዊ የሃይል ሚዛን ለኢትዩጵያ እንዳደላ በግልጽ የሚታይ ስለሆነ ኤርትራ መንግስት ሚዛኑን አዛብቶ ለኢትዩጵያ በቀጥታ አደጋ ሊሆን አይችልም ፥ የግንቦት 7 ና የአርብኞች ግንባር ውህደትም ሆነ ዛቻ ቱሻ ነው"
ይላሉ።

እነዚሁ ሰዎች ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ የኢትዩጵያ መንግስት የድንበሩን ውሳኔ እንዳለ ቢፈጽም በኢትዩጵያ ላይ የሚደርስ የጎላ ችግር እንደሌለ እንዲያውም የኢትዩጵያ መንግስት በያዘው ከገፋበት በተቃራኒው ሃገሪቱን ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል ይናገራሉ። የሚገርመው ነገር ጉዳቶች የሚሏቸው የኤርትራም ጉዳት ተብለው ከላይ ከተዘረዘሩት ጋር ይመሳሰላሉ።

እነዚህም ፦
"የያዝነውን መሬት በድንበሩ ኮሚሽን ውሳኔ መሰረት በመጨረሻ እንለቃልን። እስክንለቅ ድረስ ድንበር አካባቢ ለሰፈሩት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮች ደሞዝ፤ አበልና ለሚይዙት መሳሪያ ከፍተኛ ወጪ እናደርጋለን። ጊዜ ሳናጠፋ በአማራጭ ወደብ በመጠቀም የኪራይ ክፍያ መቀነስ አንችልም። በድንበር አካባቢ በንግድ መጠቀም አንችልም። ድንገትየተቋረጠውን የታሪክ፤ የባህልና የሶሻል ግንኙነቶች መጠገን አይታሰብም። ዘላቂ የቅርብና የሩቅ ጠላቶች በማበራከት ሃገሪቱን እናስከብባልን። ሩቅ ሊሄዱ ላማይችሉ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ድግፍ ገንዘብ እናባክናለን"
የሚሉ ናቸው። 

ይህም ሆኖ የኤርትራው ፕሬዚዳንት በኢትዩጵያ እንዲደረግ የሚፈልጉት የመንግስት ለውጥ ካልተካሄደ ባድመን ማስረከብም ሆነ ውሳኔውን እንዳለ መፈጸም ለሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች የሚሰጠው ጥቅም የለም:: 

የድንበሩ ችግር አለመፈታት ከላይ ያየናቸውን ተመሳሳይ ጉዳቶች በኤርትራም በኢትዩጵያም መንግስታትና ህዝቦች ላይ ማስከተላቸው ግልጽ ነው። መንግስታቱ ጉዳቶቹን አያውቁም ወይም ዋጋ አይሰጧቸውም ማለት ያስቸግራል። የችግሩ አለመፈታት “የቅን ልቦና” መጉደል ነው በሚል የሚዘጋም አይደለም።ችግሩ ጉልቤ የመሆን ነገር ነው።





የኤርትርው የጉልበት ችግር አፈታት፥


የኤርትራ መንግስት በ 1991 / 1993 ወደስልጣን ከመጣ ጀምሮ የድንበርን ጉዳይ በሃይል ለመፍታት መሞከሩ ተስተውሏል። ከየመን፥ ከጅቡቲና ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ በጦር ሃይል ለማስከበር ሞክሮ ሲያቅተው ብቻ ነው ወደ ገላጋዩች የሄደው። ከየመን ጋር ያለውን የወደብና የባህር ሽፋን ድርሻ ግጭት በዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ፈቷል። ይህም ሆኖ በመቶ የሚቆጠሩ የየመን አሳ አስጋሪዎች ድንበር አለፉ በሚል ኤርትራ ውስጥ በእስር ላይ ሲሆኑ ጀልባዎቻቸውም ተወርሰዋል። በጅቡቲም በኩል ያለው የድንበር ግጭት ከቆመ በኋላ በሶስተኛ ወገን አማካይነት ንግግር እየተደረገ ሳለ ኤርትራ ድንበሯ አካባቢ የነበሩ የጅቡቲ የወታደር ፖስቶች ማጥቃቷና ወታደሮች አፍና መውሰዷ ተዘግቧል። በወቅቱ ግጭቱ ቢቀጥል ጅቡቲን ለመርዳት ኢትዩጵያ ጣልቃ ልትገባ እንደምትችል ተገልጾም ነበር። በሱዳን በኩል ስላለው ሁኔታ ብዙ አይሰማም።በዚህ ላይ ለሱማሊያና ሌሎች አሸባሪዎች መጠለያና ድጋፍ በመስጠት ክስ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔና እቀባ ተጥሎበታል።

ወደኢትዩጵያ ስንመጣ የካሳ ኮሚሽኑ ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ን እንደጣሰና ኢትዩጵያን እንደወረረ አረጋግጧል። ይህ የድንበር ኮሚሽኑም እምነት እንደሆነ እንገምታለን። ከወረራው በፊት ያሉት ዓመታትም ቢሆኑ ከወረራው ባላነሰ ሁኔታ በኢትዩጵያና በዜጎቿ ላይ የኢኮኖሚና ሌሎች ጉዳቶች መድረሳቸው ይታወቃል። አንዳንዶች ጉዳቶቹን የሰላሳው ዓመት የመገንጠል ጦርነት አካል አድርገው መቁጠራቸው ያለምክንያት አይደለም።


አሁንም ቢሆን  ካላይ በተደጋጋሚ እንዳነሳነው የኤርትራው ፕሬዚዳንት በኢትዩጵያ እንዲደረግ የሚፈልጉትን የመንግስት ለውጥና ሌሎች ለውጦች መቅረታቸው  ግልጽ ካልተደረገ ችግሩ መቀጠሉ አይቀርም:: 


የኢትዩጵያ ፈተና፥ ምን ይሻላል?



በቅርቡ የተነበበ አንድ ጽሁፍ ኤርትራን የክፍለ ዘመኑ የኢትዩጵያ ፈተና ብሎ ሰይሟል። ኤርትራውያኑ ጣልያን ኢትዩጵያን ሁለቴ በወረረ ግዜ የሰጡትን ወታደራዊ አገልግልት ደማምሮ ችግሩን ወደ መቶ ምናምን ዓመታት ከፍ አድርጎታል። ይህ አልበቃ ብሎት አሁን ኢትዩጵያ ለምትገኝበት የኢኮኖሚ ድቀት ኤርትራን ይከሳል። ችግሩን ለዘለቄታው እንዴት መፍታት እንደሚቻል ማሰብ ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነም ይናገራል። በዚህ አስተያየቱ እኛም እንደግፈዋለን።

የኋለኛውን ግማሽ ብቻ ብናይ የራስ ሃገር ለማግኛት የሰላሳ ዓመት ጦርነት፥ ድንበር ለመለየት የሁለት ዓመት ጦርነት፥በጦርነት ውጤት ስላልተገኘ ለሌላ ጦርነት ለአስራ አምስት ዓመታት በተጠንቀቅ መቆም፥ በተጠንቀቅ መቆም ሲደክም ኢትዩጵያውያንን አደራጅቶ ለጦርነት መላክ። ይህ ካልተሳካ ምን ይሞክሩ ይሆን? ሌላ ጦርነት?




በአሁን ወቅት (በፊትም ቢሆን) ለኤርትራ ህዝብ የሚጠቅመው ከኢትዩጵያ ጋር ያለውን የድንበር ችግር በመነጋገር በመፍታት ሙሉ የዲፕሎማሲ፣ የወደብና የንግድ ስምምነቶች በመፈራረም ከፍታኛ ገቢ በማግኘት የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው። ወታደራዊ ውጥረቱና አተካራው ለሁለቱ ሃገሮችና ህዝቦች ያስገኘው ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለም። ስንት መንገድ፣ ትምህርት ቤትና ክሊኒኮች ሊክፍት የሚችል ገቢ ቀረ? ወደፊትስ ይቀራል?

ጎበዝ! ጉዳቱ የገባን ኢትዩጵያውያንና ኤርትራውያ ተረዳድተን አንድ እንበላቸው::

በቸር ይግጠመን። 

GLOBAL CONFLICT AND DISORDER PATTERNS: 2020

This paper was presented at the 2020 Munich Security Conference at a side event hosted by the Armed Conflict Location & Event D...