Tuesday, June 4, 2019

የኢትዩጵያና የኤርትራ ጦርነት የጉዳት ካሣ ጉዳይ፤

(Assistant editor's note: The following is a reprint of a commentary published on our blog spot in November 2013 regarding the rulings of the Eritrea - Ethiopia Claims Commission rendered in August, 2009. The commentary is a summary of an extensive report prepared by researchers of Entoto Forum for Social Justice (EFSJ). We are reprinting it because so many Ethiopians as well as Eritreans seem uninformed as to what the claims of Eritrea and Ethiopia were and how their claims were decided. It is a complete review of the claims process including the untold damage caused by the governments of Eritrea and Ethiopia on one another and the sufferings they caused to their respective populations. The commentary gives a good backrgound information on the issue even if some of its references are a couple of years old. 

EFSJ researchers have also studied the decision of Eritrea - Ethiopia Boundary Commission. A summary of their study has been published on this blog spot under the title ኤርትራ - ለራሷ ያልሆነች ሃገር፣ የኢትዩጵያ ፈተና  a while ago. In that report, they have emphasized that the stalemate between Eritrea and Ethiopia is costing them dearly in economic and other respects, but the cost can be mitigated and even reversed to mutual benefit if Ethiopia complies with Eritrea's demands and take the initiative to implement the rulings.)

___________________________________________________  


የኢትዩጵያና የኤርትራ ጦርነት የጉዳት ካሣ 


በሲቲና አህመድና ጓደኞቿ siti-ahmed@gmail.com )


     1.   የኢትዩጵያና የኤርትራ የካሣ ኮሚሽን ውሳኔና የሃገራቱ ምላሽ
     2.   የኮሚሽኑ ውሳናኔ መጠንና የኢትዩጵያ ባዶ እጅ መቅረት    
     3.   ሃገራቱ አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱት በማሰረጃ የተረጋገጠ ውድመት
         -  የጉዳቶች ዝርዝርና አይነት
         - በወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳትና የጦርነቱ ወጪ ምስጢርነት      
     4.   የኢትዩጵያና የኤርትራ የካሳ ጥያቄ መጠንና የኮሚሽኑ ውሳኔ
     5.   የህግ ምክርና የጥብቅና አገልግሎት ቸግሮች
     6.   የኢትዩጵያና የኤርትራ የካሣ ኮሚሽን ውሳኔና የመንግስታቱ አቋም
     7 .  የካሣውን ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰላማዊ ሰዎች ማዋል
     8.   በኤርትራ ላይ ብቻ የተጣሉ የመሣሪያና ሌሎች ዕቀባዎች
     9 . ምን ቢደረግ ይሻላል?
________________________________________________




መግቢያ፤



የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ አልጀርስ ላይ በኢትዩጵያና በኤርትራ መሪዎች መካከል ታህሳስ 2000 ላይ በተደረገ ስምምነት የተቋቋመው የካሣ ኮሚሽን የሰጠውን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ሊረሳ ምንም ያልቀርውን የሁለቱን ሃገሮች መሪዎች፤ ገዢ ፓርቲዎችና መንግስታት የጥፋት ድርጊት ማስታወስና ጦርነት እንዳይደገም ነቅተን እንድንጠቅ  እንዲሁም በመሪዎቹ መካከል እርቅ ወረዶ የሁለቱም ሃግሮች ሕዘቦች የሰላም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድምጻችንን እንድናሰማ ማሳሰብ ነው። ኮሚሽኑ ሁለቱ ሃገሮች ከግንቦት 1998 እስከ ሰኔ 2000 ባካሄዱት ጦርነት አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱትን ጉዳት በመለየት አንዳቸው ለሌላው ሊከፍል ይገባል ያለውን የካሣ መጠን በመወሰን ሥራውን ነሓሴ 17/ 2009 አጠናቋል። የድንበር ኮሚሸኑም እንደዚሁ የሁለቱን ሃገሮች ድንበር አካልሎ በምድር ላይ ምልክት ከማቆም ያላነሰ ውጤት ያለው ድንበር በወረቀት ላይ በማስፈር ስራውን ኅዳር 2007 ላይ ፈጽሟል።


በጽሁፉ በቅድሚያ ኢትዩጵያ ከኤርትራ ጋር በነበራት የካሣ ክርክር እንዴት ባዶ እጇን እንደወጣችና እናያለን። ይህ የሆነበት ምክንያት በክፊል ስልጣን ላይ በነበሩ እና አሁንም ባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ድክመት ሲሆን የተቀረው ደግሞ በኤርትራ ጥንካሬ ምክንያት ነው። በመቀጠል በዋነኛነት የኢትዩጵያና የኤርትራ መንግስታት ለካሣ ኮሚሽን ያቀረቡትን የካሣ ይገባኛል ጥያቄና ያያዙዋቸውን ማስረጃዎች በማዛመድ አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱትን የጉዳት መጠን፤ በኮሚሽኑ የካሣ ውሳኔ ላይ ሁለቱ መንግስታት የያዙትን አቋምና አቋማቸው ያስከተለውን ውጤት፤ ኮሚሽኑ ለመንግስታቱ አነስተኛ የካሣ ገንዘብ እንዲከፈል የወሰነበትን ምክንያት፤ ስለአካፋፈሉ ሁኔታ የገለጸውንና ገንዘቡን እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሃሳብ እንመረምራልን።  የድንበሩም ሆነ የካሳው ጉዳይ እስከ አሁን እልባት ባለማግኘታችው ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ መኖር አለምኖሩን ለማሳየት እንሞክራለን። በመጨረሻም ምን ቢደረግ እንደሚሻል እናነሳለን።

በቀንና ዓመት አጠቃቀስ ላለመሳሳት ስንል የአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ስለተጠቀምን ይቅርታ እንጠይቃለ::



1. የኢትዩጵያና የኤርትራ የካሣ ኮሚሽን ውሳኔና የሃገራቱ ምላሽ፤


Image result for eritrea and Ethiopiaሁላችንም እንደምናስታውሰው የካሣ ኮሚሽኑ ውሳኔውን የዛሬ ዘጠኝ አመት አካባቢ ሲያስታውቅ የኢትዩጵያና የኤርትራ መንግስታት ውሳኔው አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል። የኢትዩጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ባወጣው መግላጫ ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ ባሳለፈው ውሳኔ ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ን እንደጣሰችና ኢትዩጵያን እንደወረረች ማረጋገጡን አስታውሶ ለኢትዩጵያ እንዲከፈል የታዘዘው ገንዘብ ከደረሰው ጉዳት ጋር ሲመዛዘን አነስተኛ መሆኑን ገልጿል። በመጠረሻም ውሳኔውን እንደሚያጠናው አመልክቶ ኤርትራ ለኢትዩጵያ መክፈል ያለባትን ክፍያ የምትፍፈጽምበትን ሁኔታ እንደሚከታተል አስታውቋል። ውሳኔው ከተሰጠ ዘጠኝ አመታት ቢያልፉም መንግስት ጥናቱን ጨርሶ ውሳኔውን መቀበል ወይም አለመቀበሉን፤ ስለክፍያውም ያደረገውን ክትትል አላሳወቀም።


የኤርትራ መንግስት በበኩሉ የድንበሩ ጉዳይ በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሰረት ሳይፈጸም እስከአሁን መቆየቱ ትክክል አለመሆኑን ገልጾ የካሣውን ውሳኔ ግን እንደተቀበለ አስታውቋል። የኢትዩጵያ መንግስት በድንበሩ ውሳኔ ወቅት ግልጽ አቋም መያዝ እንዳቃተው ሁሉ በካሣው ውሳኔም እንደተቸገረ ይታያል። ቢሆንም ውሳኔው ከተሰጠ ዘጠኝ አመታት ሲያልፉ አንዳችም ውሳኔውን የመቃወም ድምጽ ባለማሰማቱ ውሳኔውን በዝምታ እንደተቀበለ ይቆጠራል። የኤርትራ መንግስት በድንበሩ ውሳኔ ላይ እንዳደረገው ሁሉ የካሣውም ውሳኔ እንደተሰጠ ወዲያው ተቀብሏል።



2. የኮሚሽኑ ውሳኔ መጠንና የኢትዩጵያ ባዶ እጅ መቅረት፤

 
Image result for empty handedየኢትዩጵያንና የኤርትራን መንግስታት መሪዎች፤ ገዢ ፓርቲዎችና መንግስታት ሃላፊነት የጎደለው የጦርነት ተግባር፤ ምናልባትም የመሪዎቹን የወንጀል ድርጊትና ከጦርነት የማትረፍ ፍላጎት በማየት ይመስላል ኮሚሽኑ የኢትዩጵያ መንግስት ሊከፈለኝ ይገባል ካለው 14. 3 ቢሊዩን ዶላር ውስጥ እጅግ ከፍታኛውን እጅ ውድቅ በማድረግ 174 ሚሊዩን ዶላር በኤርትራ መንግስት እንዲከፈለው፤ የኤርትራ መንግስት ደግሞ ሊከፈለኝ ይገባል ካለው 6 ቢሊዩን ዶላር ውስጥ እንዲሁ እጅግ ከፍታኛውን እጅ ውድቅ በማድረግ 163 ሚሊዩን ዶላር በኢትዩጵያ መንግስት እንዲከፈለው ወስኗል። አንዱ መንግስት ለለላው እንዲከፍል የተወሰነው ዕዳ ቢቻቻል የኢትዩጵያ መንግስት ከኤርትራ መንግስትላይ 10 ሚሊዩን ዶላር ይፈልጋል::

የመንግስታቱ መሪዎች ህዝቦቻቸውን አጣልተው ማጫረስና ንብረታቸውን ማውደም ብቻ ሳይሆን በሚፈራረሙትም ስምምነት መሠረት የሚፈጽሙት ምንም ነገር የለም። የካሣ ኮሚሽን ውሣኔ እንደድንበሩ ውሳኔ አስገዳጅና የመጨረሻ ነው። ሆኖም በውሰኔው መሰረት የሚደረግ ክፍያ ወይም ማካካስ ካለ እስከአሁን አልተደረገም። ክፍያ ወይም ማካካስ ካለ ያልነው እስከጭራሹ የሚከፈልም የሚካካስም ገንዘብ መኖሩ አጠራጣሪ ስለሆነ ነው። ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው።

አንደኛ፤ በጦርነቱ ወቅት በጸጥታ (security) ምክንያት ከኢትዩጵያ እንዲወጡ የተደረጉ ኤርትራውያንና በአንድ ወገን ኢትዩጵያዊ በሌላ ወገን ደግሞ ኤርትራዊ የሆኑ ሰዎች ንብረታቸውንና ገንዘባቸውን ይዘው እንዲሄዱ አልተፈቀደላቸውም። የኤርትራ መንግስት እነዚህ ሰዎች ትተውት የወጡት ንብረት ግምትና ገንዘብ እንዲከፈለው በጠየቀው መሰረት 46 ሚሊዩን ዶላር ተፈቅዶላታል። ይህ ገንዘብ ለኤርትራ እንዲከፈል በታዘዘው 163 ሚሊዩን ዶላር ውስጥ ተይዟል። በአንጻሩ ከኤርትራ እንዲወጡ ለተደረጉ ኢትዩጵያውያን የተፈቀደው 3 ሚሊዩን ዶላር ብቻ ነው። ይህ ገንዘብ ኤርትራ ለኢትዩጵያ እንድትከፍል በታዘዘው 174 ሚሊዩን ውስጥ የተጠቃለለ ስለሆነ ኤርትራ ከኢትዩጵያ የምትፈልገውን 43 ሚሊዩን ዶላር በማቻቻል አግኝታለች።

በሌላ በኩል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከኢትዩጵያ እንዲወጡ የተደረጉ ኤርትራውያን ወደ ሃገር በመመልስ ንብረታቸውን፤ ንብረቱ ከተሸጠም ዋጋውን መውሰድ እንደሚችሉ የካሣው ውሳኔ ከመታወቁ ሁለት ወራት ቀደም ብሎ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ ሆናል። መንግስት ሰዎቹ ንብረታቸውን ወይም ገንዘባቸውን የሚያገኙበትን መንገድ ስለዘረጋሁ ለኤርትራ መንግስት የምከፍላው ገንዘብ የለም ባይ ነው። እኛ በማካካስ ከፍለሃል ነው የምንለው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ መመሪያው ከኮሚሽኑ ውሳኔም በኋላ አልተሻረም ነበር። የኤርትራ መንግስት ለኢትዩጵያውያን የዚህ ዓይነት ዕድል አልሰጠም። ዜጎቹ ግን ለመንግስታቸው በማካካስ የተከፈልውን ገንዘብ ከመውሰድ ይልቅ ወደ ኢትዩጵያ እየመጡ ወይም በወኪሎቻቸው አማካይነት ገንዘብና ንብረት ወስደዋል። በአንድ በኩል መንግስታቸው ዕዳውን በማቻቻል የተከፈለው ሲሆን በሌላ በኩል ደግም ራሳቸው እየቀረቡ ንብረት ወይም ገንዘብ ሲረከቡ ለአንድ ጉዳት ሁለት ካሣ አገኙ ማለት ነው።

ሁለተኛ፤ በጦርነቱ ወቅት አሰብና ምጽዋ ላይ የነበረ ዋጋው 117 ሚሊዩን ዶላር የሆነ (135,000 ቶን ደረቅ ራሽን፤ 33 ሚሊዩን ሊትር ነዳጅ፤ 1,400 አዲስ ተሽከርካሪዎች፤ ወዘተ) የተዘረፈ ወይም ሳይወሰድ ሜዳ የቀረ የኢትዩጵያ መንግስት፤ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የንግድ ድርጅቶችና የግለሰቦችን ንብረት ነበረ። የኢትዩጵያ መንግስት ይህን ጉዳይ መከታተል እርግፍ አድርጎ የተወው ገና ከመነሻው ነው። ይባስ ብሎም ንረታቸውን የተዘርፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፤ የንግድ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን የምችለውን ሁሉ አድርጌ ስላልተሳካልኝ አርፋችሁ ተቀመጡ  ብሏቸዋል። ይህን ያለው ሰዎቹ የንብረታቸውን ዋጋ ለማስከፈል በሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ሃገር ሊወስዱበት የሚችሉት ህጋዊ እርምጃ አለመኖሩን ስለሚያውቅ ነው። ለነገሩ ኮሚሽኑ የኤርትራ መንግስት በዚህ ንብረት ጉዳይ እንደማይጠየቅ የወሰነው ታህሣስ 2005 ላይ ነው። ኮሚሽኑ ለዚህ ውሳኔው መሰረት ያደረገው በኢትዩጵያ መንግስት የቀረበለትን የባህር ትራንዚት ኢንተርፕራይዝ ያዘጋጀውን የንብረት ዝርዝር ሲሆን ማስረጃው የኤርትራ መንግስትን ጥፋት ከሚያሳይ ይልቅ የኢትዩጵያ መንግስት ንብረቱን ለመረከብ በወቅቱ ችግር እንዳልነበረበት የሚያሳይ ነው በሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ መንግስት በክርክሩ ወቅት የኢትዩጵያ መንግስት አሁንም ንብረቱን መውሰድ ይችላል፤ እንዳይበላሽ በመስጋት የሽጥኩትም ገንዘብ ስላለ እሱንም ጨምሮ ይውስድ ብሎ ነበር። መንግስት ግን በዚህ ጉዳይ ያደረገው ክትትል አልነበረም። ትክክለኛው አሰራር አግባብ ያለው ማስረጃ በማቅረብ ካሣ ማስወሰን ፤ ካልተቻለም ንብረቱን ወይም ገንዘቡን ከኤርትራ በማምጣት ለባለንብረቶቹ ማስረከብ ነበረ። ይህን አለማድረጉ እጅግ የሚሳዝን ነው። ከካሣው ውሳኔ በኋላ በውሳኔው ጥናት ተጠምዶ በማካካስ የሚፈልገውን 10 ሚሊዩን ዶላር የሚያገኝበትን መንገድ ሲያሰላስል ይመስላል ሃያ ጊዜ እጥፍ የሆነ የበሰለ ገንዘብ አምልጦታል።

ለተመላሽ ኤርትራውያን የሚመለሰው ንብረት ግምት ወይም የሚከፈላው ገንዘብ 43 ሚሊዩን ዶላር (46 ሚ - 3ሚ = 43 ሚ) ወደብ ላይ ቀልጦ ከቀረው ንብረት ግምት 117 ሚሊዩን ዶላር ጋር ሲደመር የኢትዩጵያ መንግስት በካሣ ኮሚሽኑ እንዲከፈለው የታዘዘለትን 174 ሚሊዩን ዶላር ሊያጣፋው ምንም አይቀረውም። የኤርትራ መንግስት በበኩሉ 163 ሚሊዩን ዶላር ኤርትራውያን ኢትዩጵያ መጥተው የወሰዱት ወይም የሚወስዱት ንብረት ወይም ገንዘብ ሳይቀነስ እንዲሁም ወደቦቹ ላይ ለቀሩት ንብረቶች ግምት ምንም ሳይከፍል እንደዘበት 163 ሚሊዩን ዶላር በእጁ ላይ ቀረለት ማለት ነው። በዚህ ስሌት መሰረት የኢትዩጵያ መንግስት ከካሣው ውሳኔ የሚያገኘው አንዳችም ገንዘብ ካለመኖሩም በላይ የኤርትራ መንግስት በዚያው መጠን ተጠቅሟል። እንግዲህ በመንግስት ድክመት ምክንያት የካሣ ገንዘብ ቀልጦ የሚቀርው እንደዚህ በመሰለ ሁኔታ ነው።



3. ሃገራቱ አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱት በማሰረጃ የተረጋገጠ ውድመት ፤



እኛ እንደሚገባን የካሣው ውሳኔ ዋና ጠቀሜታ የካሳው ክፍያ ሳይሆን የኢትዩጵያና የኤርትራ መንግስታት ወታደሮች ሥልጣን ላይ በነበሩና አሁንም ባሉ መሪዎች ትዕዛዝ በህይወትና በንብረት ላይ ያደረሱትን እጅግ ከፍተኛ ውድመት በጥሩ ሁኔታ መዝግቦ መያዙ ነው። ካሣ ለማግኘት ይጠቅመናል በማለት የውድመቱን መጠንና ዓይነት መንግስታቱ ራሳቸው አንድም ነገር ሳይደብቁ በዝርዝር በማስረጃ አስደግፈው ያቀረቡት ስለሆነ እውነትነቱ አያጠራጥርም። የኢትዩጵያ መንግስት ያደረሰውን ውድመት የኤርትራ መንግስት በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል። የኤርትራ መንግስት ያደረሰውን ውድመት ደግሞ የኢትዩጵያ መንግስት በበኩሉ በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል። በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ የትም ሳይሄዱ መንግስታቱ ያቀርቡትን ማስረጃ ከመንግስታቱ ወይም ከኮሚሽኑ መዝገብ ቤት መመልከት ይበቃቸዋል።

Image result for ethiopia eritrea destructionበድምሩ ሲታይ አንዳቸው በሌላው ላይ ያደረሱት ውድመት ዘግናኝና ወደፊትም እንደዚህ ያለ ጦርነት መደገም ሳይሆን መሞከር የማይገባው መሆኑን ያስገነዝባል። ከደረሰው ውድመት አንጻር ሲታይ ጦርነቱን የጀመሩትም ሆኑ በመከላከል ሰበብ ወረራ እንዲካሄድ ያዘዙ መሪዎች እንዲሁም ትዕዛዙን ተግባራዊ ያደረጉ ሰዎች አሁንም ስልጣን ላይ መሆናቸው ይገርማል። ሃገሮቹ ኢትዩጵያና ኤርትራ ሆነው ነው እንጂ በሌላ ሃገር ቢሆን በድርጊታቸው ተዋርደው፤ ከስልጣን ተባረው በወንጀል በተጠየቁ ነበር።

የግንቦት 1998 የኤርትራ መንግስት ወረራ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው የኤርትራ መንግስት በአሜሪካና በሩዋንዳ የቀረበውን ባለአራት ነጥብ የሰላም ዕቅድ ውድቅ ካደረገ በኋላ የካቲት 1999 ላይ ሁለቱም ሃገሮች አውሮፕላን ተጠቀመው ከተማዎችን በመደብደብ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ ነው። በዚሁ ወር የኢትዩጵያ መንግስት የኤርትራን የተጠናከሩ መከላከያ ምሽጎች ሰብሮ በማለፍ አስር ኪሎ ሜትር ኤርትራ ክልል ከገባ በኋላ የኤርትራ መንግስት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ/አ/ ድ/) የሰላም እቅድ ተቀብያልሁ አለ። የኢትዩጵያ መንግስትም የሰላሙን እቅድ ተቀብያልሁ ቢልም የኤርትራ መንግስት ሰራዊቱን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወደነበረበት ቦታ እስኪመለስ ድረስ ይዞታውን ማስፋፋት ቀጠለ። የኤርትራ መንግስት ወደመሸነፉ ሲቃረብ የአ/ አ/ ድ/ ን የሰላም እቅድ መቀበሉን እንደገና አስታወቀ። የኢትዩጵያ መንግስት አወዛጋቢ የሆኑትን ቦታዎች በሙሉ ከያዘና የኤርትራ መንግስትም በ አ/ አ/ ድ/ ዕቅድ መሰረት ጦርነቱ ሲጀመር ወደነበረበት ቦታ እንደሚመለስ ካረጋገጠ በኋላ ጦርነቱ አብቅቷል አለ። በዚህ ወቅት የኤርትራን መሬት አንድ አራተኛ ይዞ ነበር።




የጉዳቶች ዝርዝር አይነትና መጠን፤  



Image result for ethiopia eritrea mutual destructionወደ ጦርነቱ ጉዳት ስንመለስ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የኢትዩጵያ መንግስትና የኤርትራ መንግስት ጦርነት በተገኘው ነገር ሁሉ በመጠቀም የተካሄደ ሆኖ እንገኘዋለን። የኢትዩጵያ መንግስት ለካሣ ኮሚሽኑ ባቀረበው የካሣ ጥይቄ ተፈጸመብኝ ያለውን በደል በማስረጃ ለማሳየት ያቀረባቸው ሰነዶች ጣሪያ ይነካሉ። ኮሚሽኑ የኢትዩጵያ መንግስት ደረሰብኝ ያለውን ጉዳት ካቀረበው ማስረጃ ጋር ካገናዘበ በኋላ የኤርትራ መንግስት በድንበር አካባቢ ያሰማራቸው ወታደሮች ጉዳት ሲያደርሱ ባለማስቆሙ ጥፋተኛ አድርጎታል። አስከትሎም የኢትዩጵያ መንግስት ያቀረበውን የጉዳት ዓይነትና መጠን በከፊል በመቀበል የገንዘብ ካሣ ፈቅዷል።

የኢትዩጵያ መንግስት በካሣ ጥያቄው ላይ የኤርትራ ወታደሮች በማዕከላዊ ፤ በምዕረብና በምስራቅ ግንባሮች ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል፤ ደብድበዋል፤ አስረዋል፤ ጠልፈዋል፤ አስገድደው የጉልበት ሥራ አሰርተዋል፤ ንብረት ዘርፈዋል፤ አውድመዋል፤ ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል፤ ስለ እስረኞች መረጃ ከልክለዋል ብሏል። እነዚህ ጉዳቶች የተፈጸሙበት ሰላማዊ ህዝብ ቁጥር 242, 000 መሆኑን (ቁጥሩ 350, 000 የተፈናቀሉ ሰዎችን አይጨምርም) ፤ ከዚህ ውስጥ 13, 394 (በኋላ ቁጥሩ ወደ 54, 000 ከፍ ተደርጓል) ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ (ቁጥሩ በተቀበሩ ፈንጂዎች የሞቱ 124 ሰዎችን አይጨምርም) ፤ 83, 000 ድብደባና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ( አሁንም ቁጥሩ በተቀበሩ ፈንጂዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን 340 ሰዎች አይጨምርም) ፤ 20, 354 የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ፤ 9, 443 በግዳጅ ሥራ እንደተሰማሩ፤ 236 ሴቶች ተገድደው እንደተደፈሩ፤ 16, 400 (በኋላ ወደ 77, 000 ከፍ የተደረጉ) ቤቶች እንደተጎዱ ወይም እንደፈረሱ፤ ወዘተ. ጨምሮ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የመንግስትን ንብረት በሚመለከት 331 ህንጻዎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ክሊኒኮች፤ የውሃ መስመሮች፤ የእርሻ ማሰልጠኛ ተቋሞች ፤ ወዘተ መዘርፋቸው ወይም መውደማቸው፤ 164 ቤት ክርስቲያኖችና ገዳማት፤ መስጊዶች፤ ቤት ክርስቲያኖች የሚያስተዳድሯቸው ክሊኒኮች ወዘተ መዘረፋቸውን ወይም መውደማቸውን አስረድቷል። የሳባ ማርብልስ ማሺነሪዎች ተነቅለው ወደ ኤርትራ መወሰዳቸውን ጨምሮ አሳይቷል። ቀይ መስቀል ማህበር ኢትዩጵያዊ የጦር ምርኮኞችን እንዳይጎበኝ ኤርትራ እንዳደረገ፤ ከዚህም በላይ የኢትዩጵያ ወታደሮች ከተማረኩ በኋላ ግድያ፤ ድብደባ፤ ቅሚያ፤ ጉስቁልና፤ ጤናን ላደጋ ማጋለጥ፤ አስገድዶ ማሰራት ፈጽሟል በማለት ከሷል። ጦርነቱ ሲጀመር ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 120, 000 ሰላማዊ (ሲቪል) ኢትዩጵያውያን ማስፈራራት፤ ድብደባ፤ ግድያ፤ በሥራ ቅጥርና በህክምና አግልግሎት ልዩነት ማድረግ፤ ከህግ ውጭ እስራት፤ ንብረት መቀማት፤ ከሃገር ማስወጣት ወዘተ. እንደደረሰባቸው አሳይቷል። የኤርትራ መንግስት የዲፕሎማቲክ ጥበቃ ያላቸው ንብረቶች፤ መጻጻፎች፤ ባዶ ፓስፖርቶች ወስዷል፤ ሻርዥ ዳፌር አስሯል። ከዚህ በተጭማሪ የኤርትራ መንግስት ወደቦቹ ላይ የነበሩ ቁሳቁሶች እዚያው በማስቀረት እንዲዘርፍ ወይም እንዲበላሽ፤ የኢትዩጵያ አየር መንገድ ኪሳራ እንደደረሰበት ፤ በጦርነቱ ምክንያት ቱሪዝም፤ ንግድ፤ የውጭ እርዳታ፤ እንቬስትመንት በመታጎላቸው የኢኮኖሚ ጉዳት እንደተከሰተ፤ ታክስ ሳይሰበሰብ እንዲቀር ምክንያት እንደሆነ አስረድቷል። የኤርትራ መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን እንደገና ለመገንባት ገንዘብ ወጪ እንዲሆን ፤ በተፈጥሮ ሀብትና በአካባቢ ጤና ላይ ጥፋት በማድረስ ጥፋቱን ለመገምገምና ለመመዝግብ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንዲደረግ አስገድዷል።

የኤርትራ መንግስትና ህዝብ በኢትዩጵያ መንግስት ወታደሮች የደረሳባቸው ሰፊ ጉዳት እነርሱ በኢትዩጵያ ላይ አድርሰዋል ከተባሉት ተመሳሳይ ናቸው። የካሣ ኮሚሽኑ ለኢትዩጵያ መንግስት እንዳደረገው ሁሉ የተዘረዘሩት ጥፋቶች በኢትዩጵያ ወታደሮች መፈጻማቸውንና ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል። አስከትሎም የኢትዩጵያ መንግስት የወታደሮቹን የጥፋት ድርጊት ባለማስቆሙ ለኢትዩጵያ መንግስት ከፈቀደው ካሣ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ ለኤርትራ መንግስትም ፈቅዷል። የኢትዩጵያ መንግስት ወታደሮች ካደረሱት ጉዳት ውስጥ ጥቂት ለመግለጽ ያህል ፡ - በመካከለኛውና በምዕራቡ ግንባር የንብረት ዘረፋ፤ በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረስ፤ የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስ፤ ማቃጠል፤ ሰብሮ መግባት፤ የቤት እንሰሳት ዘረፋ፤ ሴቶች መድፈር፤ ህንጻዎች (የመንግስትን፤ የንግድና የግል) ማውደም፤ የጤና ጣቢያዎች፤ ሆቴሎችና ትምህርት ቤቶች መፋረስ፤ የጥጥ ፋብሪካ ማቃጠል፤ የትምባሆ ኩባንያ ማሰናከል፤ የሃይማኖትና የባህል ንብረቶችን ማባላሸት እንደጥፋት ተዘርዝረዋል። ከጉዳቱም የተነሳ የሥራ፤ የትምህርት፤ የስልክ፤ የውሃ፤ የመብራትና የጤና አገልግሎት መሰናከላቸው ተገልጿል። የጦር ምርኮኞች ድብደባ፤ ዘረፋ፤ ጤና ማጓደል፤ የምግብ እጥረት፤ የፖለቲካ ሰበካ እንደተካሄደባቸው ተመልክቷል። ከዚህ ሌላ ከፍታኛ የሆነ የሰላማዊ ህዝብ መፈናቀል፤ ህገወጥ የሆነ የኢትዩጵያ ዜግነት ገፈፋ፤ ንብረት ያለህግ ማጣት፤ ከሃገር ማስወጣት፤ ተሽከርካሪዎች መያዝ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃን አለማክበርም ታይቷል።

እዚህ ላይ መገንዘብ የሚያስፈልገው የኤርትራ መንግስት የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር በመጣስ ጦርነት የቀሰቀሰ መሆኑ በኮሚሽኑ ቢረጋገጥም የኢትዩጵያ መንግስት የኤርትራን ወረራ ለመቀልበስና ድንበሩን ከጦረነቱ በፊት ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ባደረገው መልሶ ማጥቃት በሰላማዊ ህዝብና በንብረት ላይ የኤርትራ መንግስት በኢትዩጵያ ላይ ካደረሰው ያላነሰ፤ ምናልባትም ሊበልጥ የሚችል ጉዳት አድርሷል። በሰላማዊ ህዝብና ንብረት ላይ የሚደርስ ወታደራዊ ጥቃት የተወገዘ ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።




በወታደሮች ላይ የደረሰ ጉዳትና የጦርነቱ ወጪ ምስጢርነት፤


Image result for death of ethiopia and eritrea soldiersበወታደራዊ መስክ ካየነው የካሣው ኮሚሽን ሥራ በወታደሮችና በጦር መሳሪያዎች ላይ የደረሰን ጉዳት አያይም። ይህ ጉዳት ብርቱ ምስጢር በሚል በሁለቱም መንግስታት ታፍኗል። የኢትዩጵያ መንግስት ምን ያህል ወታደሮች እንደሞቱበትና እንደቆሰሉበት አልተናገረም፤ ወደፊትም የሚናገር አይመስልም። አንዳንድ የሴኩሪቲ ጥናቶች የኢትዩጵያ መንግስት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የዋለ “ጉድጓድ ውስጥ አድፍጦ በመጠበቅ ሁኔታው የተመቻቸ ሲመስል ግር ብሎ ውጥቶ የመጋፈጥ ውጊያ” ስልት በመጠቀም ከ 100 000 በላይ ወታደሮች እንድሞቱበትና የዛንው ያህል እንደቆሰሉበት ይናገራሉ። የኢትዩጵያ መንግስት የሞቱና የቆሰሉት ስንት እንደሆኑ ብቻ ሳይሆን ለጦርነቱ ወጪ ያደርገውን ገንዘብ መጠንም ለማሳወቅ ፈቃደኛ አይደለም። የኢትዩጵያ ኢኮኖሚክስ ሪሰርች ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱ ወጪ 2. 9 ቢሊዩን ዶላር ይሆናል ሲል የሴኩርቲ ጥናቶቹ የኢትዩጵያ መንግስት በካሣ ክርክሩ ወቅት እንዲከፈለው የጠየቀው 14. 3 ቢሊዩን ዶላር በኢትዩጵያ ላይ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በማሳየት ረገድ የሚታመን ነው ይላሉ። በድምሩ ሀገራችን በሁለት የጦርነት ዓመታት በትንሹ 17 ቢሊዩን ዶላር አጥታለች ማለት ነው። ይህ ገንዘብ የኢትዩጵያን የ 2008 GDP ሦስት አራተኛ (3/4) ይሆናል።

የሚገርመው ነገር በሁለቱ ሃገሮች ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ጉዳት ያደርሱ መሪዎችና ተባባሪዎቻቸው ለጉዳቱ በግላቸውም ሆነ በጋራ ተጠያቂ አለመሆናቸው ነው። ተጠያቂ ስላልሆኑ ከጥፋታቸው የተማሩት ነገር የለም። አሁንም ችግርን በሰላም የመፍታትም ነገር አይታያቸውም። በዚህ ሁኔታ ነገ ወይም ተነገ ወዲያ እነርሱ ራሳቸው ወይም ተከታዩቻቸው ወደ ጦርነት ቢወስዱን አይደንቅም። 



4.  የኢትዩጵያና የኤርትራ የካሳ ጥያቄ መጠንና የኮሚሽኑ ውሳኔ፤

 
Image result for claims and compensationየኢትዩጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔና ውሳኔው ያስከተለው ጦርነት ቀረሽ እሰጥ አገባ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን የድርድር (arbitration) ሥራ ከፍተኛ ቀውስ (crisis) ውስጥ የከተተ አሁንም ያልተፈታ ችግር ነው። ከውሳኔው በኋላ ጦርነት ቢከሰት ኖሮ የድርድሩ ማህበረሰብ (arbitration community) የባሰ ቀውስ ውስጥ በገባ ነበር። የካሣ ኮሚሽኑ የድንበር ኮሚሽኑ ያጋጠመውን ቀውስ ጠንቅቆ ያውቃል። የሁለቱን ሃገሮች መሪዎች ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ክብር የማይሰጡ፤ ምክሩንም ሆነ አስተያየቱን እንደድክመት የሚቆጥሩ፤ በሃገር ውስጥም ለህዝብ ተጠሪነት የሌለባቸው እንደሆኑ ይገነዘባል። ኮሚሽኑ አስር ዓመት የወሰደ የመጨረሻ ውሳኔውን ነሓሴ 17/ 2009 ሲሰጥ ውሣኔው በኢትዩጵያና በኤርትራ መካከል ሌላ ቀውስ እንዳይፈጥር ከፍተኛ ጥንቃቄ በማደረግ እንደሆነ ከውሳኔው መረዳት ይቻላል። ከጥንቃቄ ብዛት ሁለቱም ሃገሮች ከጠየቁት ካሣና ከደረሰባቸው ጉዳት የማይመጣጠን እጅግ አነስተኛ ገንዘብ ፈቅዶ፤ የገንዘቡንም መጠን ተቀራራቢ በማድረግ አንዳቸው ከሌላው የሚፈልጉትን ገንዘብ ለማቻቻል አመቺ የሚመስል ሁኔታ ፈጥሯል። ውሳኔው የሀገሮቹን ድህነትና በዓለም ዓቀፍ ህግ ከጦርነት በኋላ የሚከፈል ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን በማጉላት “አንተም ተው አንተም ተው” የሚል ዓይነት ነው። ከሙያ አንጻር ሲታይ ውሳኔው የዓለም ዓቀፍ ድርድርን ደረጃ የጠበቀ ነው ለማለት ባያስደፈርም ከተግባራዊነት (practicality) ፤ ከተፈጻሚነት (enforceability) እንዲሁም ግጭትን ከመቀነስ አንጻር ሲታይ የኢትዩጵያ መንግስትም ሆነ የኤርትራ መንግስት ያገኙት የሚገባቸውን ነው ያሰኛል።

የኢትዩጵያ መንግስትና የኤርትራ መንግስት በጦርነቱ ደረሰብን ያሉትን ጉዳትና ለጉዳቱ ይገባናል ያሉትን የካሣ መጠን በዝርዝር መመልከት ከዚያም ኮሚሽኑን የካሣ መጠን ውሳኔ ማገናዘብ ውሳኔው ማስገኘት የፈለገውን ውጤት ለመረዳት ያስችላል። እዚህ ላይ በመጀመሪያ የኢትዩጵያ መንግስት እንዲከፈለው የጠየቀውንና የተከለከለውን፤ ቀጥሎ ጠይቆ በከፊል የተፈቀደለትንና በመጨረሻ ደግሞ ጠይቆ ሙሉ ለሙሉ የተፈቀደለትን የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች በመውሰድ እንመልከት። ክፍያ ከተከለከለባቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ። የሞራል ካሣ (የተጠየቀ 5.1 ቢሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ሳይካሄድ የቀረ ኢንቬስትመንት ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 2 ቢሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ሳይመጣ ለቀረ ዓለም ዓቀፍ እርዳታ ካሣ (የተጠየቀ 1. 7 ቢሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለአካባቢ ጤናና የተፈጥሮ ሃብት ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 1. 28 ቢሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ከወደብ ላይ ሳይነሳ ለቀረ ንብረት ጉዳት ካሣ ( የተጠየቀ 117 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ከቱሪዝም ለታጣ ገቢ ካሣ (የተጠየቀ 104 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለአዲግራት ፋርማሱቲካል ፋብሪካ ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 32 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለአልሜዳ ቴክስታይል ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 30 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለደደቢት አክሲዩን ማህበር ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 36 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለመሶብ የህንጻ መሣሪያ አምራች ኩባንያ ካሣ (የተጠየቀ 18 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም)፤ ለኢዛና ማይኒንግ ካሣ (የተጠየቀ 2.2 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ ምንም) ናቸው። በከፊል ክፍያ የተፈቀደባቸው የሚከተሉትን ይጨምራሉ። ሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች ካሣ (የተጠየቀ 1. 5 ቢሊዩን ዶላር የተፈቀደ 45 ሚሊዩን)፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለደረሰ ሞት፤ አካል መጉደል፤ መሰወር፤ አስገድዶ ማሰራት ካሣ (የተጠየቀ 434 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 11ሚሊዩን)፤ ሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታና የፈራረሱ ኢንፍራስትራክቸር ግንባታ (የተጠየቀ 100 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 7. 5 ሚሊዩን)፤ በዘረፋና ማውደም ለደረሰ ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 50 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 14 ሚሊዩን)፤ ለፈራረሱ የመንግስት ህንጻዎች ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 14 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 315 ሺህ)፤ ለቤተ ክርስቲያኖች ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 9. 2 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 4. 5 ሚሊዩን)፤ የተደፈሩ ሴቶች ጉዳት ካሣ (የተጠየቀ 6. 7 ሚሊዩን ዶላር የተፈቀደ 2 ሚሊዩን) ናቸው። የኢትዩጵያ መንግስት ካሣ እንዲከፈለው ጠይቆ የጠየቀውን ሙሉ ለሙሉ ያገኘበት ሁኔታ እዚህ ግባ የማይባል ስልሆነ አልፈነዋል።

በዚህ ጉዳይ የካሣ ክፍያ ጠይቆ የተከለከለው ወይም በከፊል የተፈቀደለት የኢትዩጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን የኤርትራ መንግስትም ነው። ኮሚሽኑ ሁለቱ መንግስታት አንዳቸው ከሌላው ከፍተኛ የካሣ ገንዘብ እንዲከፈላቸው እንደጠየቁና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ለምን አነስተኛ ገንዘብ እንደፈቀደ በውሳኔው ውስጥ እንደሚከተለው ዘርዝሯል። አንደኛ፤ የዓለም ዓቀፍ ልማድ (custom) እና ውሳኔዎች (precedence) ያቋቋሙት አሰራር ከሚጠየቀው የካሣ ክፍያ ገንዘብ ውስጥ እጅግ አንስተኛውን (fraction) መፍቀድ ነው። በዚህ መሰረት ገና ከመነሻው የተጠየቀው በሙሉ እንደማይፈቀድ ኮሚሽኑ ግልጽ አድርጓል። ሁለተኛ፤ ኮሚሽኑ ካሣ የሚከፈለው የዓለም ዓቀፍ ህግን በመጣስ ጉዳት መድረሱ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ብሏል። በዚህ መሰረት ምንም ክፍያ ያልተፈቀደባቸው የካሳ ጥያቄዎች አንድም የዓለም ዓቀፍ ህግን በመጣስ አልተፈጸሙም ሁለትም ካሣ የሚያስከፍል ጉዳት አልደረሰም ማለት ነው። የህግ መጣስና ጉዳት ቢኖርም የካሣ ጥያቄው በማስረጃ ባለመደገፉ ውድቅ የሆነበት ብዙ ሁኔታ አለ። ሦስተኛ፤ ካሣ እንዲከፈል ቢፈቀድ እንኳ የሚከፈለው ገንዘብ በግድ ከደረሰው ጉዳት ጋር መመጣጠን አያስፈልገውም። የካሣው ጥያቄ የቀረበው በግለሰቦችና በንብረታቸው እንዲሁም በድርጅቶች ላይ ለደረሰ ጉዳት ቢሆንም ጠያቂዎች ራሳቸው ተጎጂዎቹ ሳይሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ (diplomatic protection) በሰጣቸው መንግስት በመሆኑ ክፍያው የሚታዘዘውም ለመንግስት ነው። በአንጻሩ የካሣውም መጠን በግለሰቦችና በድርጅቶች ላይ የደረሰን ተናጠል ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ስሌት አላደረገም። አራተኛ፤ ሁለቱም ሃገሮች ያጡ የነጡ ድሆች (ኮሚሽኑ የድሆች ሁሉ ድሆች ይላቸዋል) መሆናቸው እያታወቀ የጠያቁትን ቢሊዩን ዶላር መፍቀድ አግባብ አለመሆኑን ኮሚሽኑ እንዳመነበት ገልጿል። በኢኮኖሚም ሊያሽመደምዳቸው ይችላል ባይ ነው። አምስተኛ፤ ለፈቀደው ትንሽ ገንዘብም ቢሆን ወለድ ከልክሏቸዋል። ባጭሩ ሁለቱ ሃገሮች በጦር ሜዳ ያሳዩትን ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ መፍጨርጨር በካሣውም እንዳይደግሙት ሳያመነታ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶባቸዋል።



5.  የህግ ምክርና የጥብቅና አገልግሎት ቸግሮች፤  


Image result for Legal servicesእዚህ ላይ አንድ ሳይነሳ መታለፍ የሌላበት ጉዳይ ሁለቱን መንግስታት ያማከሩና መንግሰታቱን ወክለው ኮሚሽኑ ፊት በመቅረብ የተከራከሩት የህግ ባለሙያዎች ሁኔታ ነው። የኢትዩጵያን መንግስት የወከሉት በጄኔቭ የኢትዩጵያ የተባበሩት መንግስታት ቋሚ ተወካይ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት አንደኛ ፀሃፊዎች (አንዱ የህግ አማካሪና የካሣ ቡድን አስተባባሪ) ፤ አንድ ሦስተኛ ፀሃፊ እና ሁለት አታሼዎች ናቸው። የጀኔቫው ተወካይ ሥም በመጀመሪያ ስለሰፈረ ቡድኑን የመራው እርሱ ነው ለማለት ይቻላል። ቡድኑ ከዋሽንግተን ዲ/ ሲ/ 11 ባለሙያዎች (5 ጠበቆችና 6 ረዳቶች) ተጨምሮለት የተጠናከረ ነው፡፡ እነዚህ 11 ሰዎች በምን መለኪያ ከአንድ ሃገር፤ ከተማና ከሁለት የጥብቅና ቢሮዎች ብቻ እንደተመረጡ፤ የስልጠናቸውና የልዩ ስልጠናቸው መስክ ምን እንደሆነ፤ ምን አገልግሎት እንደሰጡና ምን ያህል እንደተከፈላቸው አይታወቅም። ለማንኛውም እነዚህ 17 ባለሙያዎች ኢትዩጵያ 14 ቢሊዩን ዶላር ካሣ ይገባታል በሚል ተከራክረው 174 ሚሊዩን ብቻ (ከጠየቁት ውስጥ ከ 5 % የነሰ) እንዲከፈል ሲፈቀድ ምን እንደተሰማቸው አውቀን ብናሳውቃችሁ ደስ ባለን ነበር። ግን ሰዎቹ በዚህ ጉዳይ አንዳችም ነገር መናገር ስለማይፈቀድላቸው ትንፍሽ አይሉም። ቢፈቀድላቸውም መናገር አይፈልጉም። አንድ የማይክዱት ነገር ቢኖር ይህ እጅግ አንስተኛ ገንዘብ የተፈቀደው በከፊል በእነርሱ ድክመት መሆኑን ነው። ተመሳሳይ ድክመት በድንበሩ ክርክር ወቅት ሃገራችንን ወክለው ኮሚሽኑ ፊት ቀርበው በተከራከሩ ጠበቆችንም ላይ ተንጸባርቋል። ይህ ጉዳይ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የምንመለስበት ይሆናል።

ኮሚሽኑ ከመጀመሪያው የካሣ ጉዳይ የሚወሰነው ታህሣስ 2000 ላይ በኢትዩጵያና በኤርትራ መካከል በተፈረመው ስምምነት አንቀጽ 5 (13) እንደተገለጸው በዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረት መሆኑን ለሁለቱም ሃገሮች ተወካይ (ባለሙያዎች) አሳውቋል። በመያያዝም ex aequo et bono የሚወሰን ጥያቄ እንደማይኖር አስጠንቅቋል። “በዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረት” የሚሰጠው የካሣ ውሳኔም የዓለም ዓቀፍ ህግ መጣስ መድረሱ ሲረጋገጥ እንዲሁም ደረሰ የሚባለው ጉዳት በበቂ ማስረጃ ሲደገፍ ብቻ መሆኑን አሳውቋል። የህግ መጣስም ሆነ ጉዳት መድረሱን የማስረዳት ግዴታ (burden of proof) የተከራካሪዎች እንደሆነም በማያሻማ ቋንቋ ነግሯቸዋል። ሆኖም ግን ከውሳኔው የምንረዳው ብዙዎቹ የካሣ ጥያቄዎች ውድቅ የተደረጉት ግልጽና አሳማኝ ማስረጃ ስላልቀረበባቸው መሆኑን ነው። ኮሚሽኑ “የዓለም ዓቀፍ ህግ ድጋፍ የሌለው የካሣ ጥያቄ”፤ “የማይታመን የካሣ ጥያቄ”፤ “(አሳማኝ) ማስረጃ ያልቀረበበት”፤ “የተጋነነ”፤ “ስህተት” “እውነት ያልሆነ” ወዘተ በማለት ያለፋቸው በሙሉ በዚህ ስር የሚገቡ ናቸው።

የካሣው ክርክር በኢትዩጵያውያን የህግ ባለሙያዎች በግንባር ቀደምትነትና በአሜሪካ ጠበቆች አጃቢነት የተካሄደ ቢሆንም ከላይ እንደተገልጸው ሃገሪቱ የሚገባትን የካሣ ገንዘብ እንዳታገኝ የበኩሉን አስተዋጻኦ አድርጓል። ባለሙያዎቹ የህግ ድጋፍ የሌለው የካሣ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ሲደረግባቸው፤ ጥያቄያችሁን በማስረጃ አላስደገፋችሁም ሲባሉ፤ እንዳጋነኑ፤ እንደተሳሳቱ፤ አልፎ ተርፎም እንደዋሹ ሲነገራቸው ወቀሳውን ፈገግ ብለው ማሳለፍ የስልጠናቸው አካልና ብዙ የሚኮሩበት ሙያ ባህል ነው። በካሣው ጥያቄና ውሳኔ ሃገሪቱ የታዘበችው ከዚህ የተለየ አይደለም። ከሙያ አንጻር ተልካሻ ሥራ ሰርተው በቢሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ ደንበኛቸውን ቢያሳጡም የደረሰባቸው ነገር የለም። የሃገር ቤቱ ባለሙያዎች ጥያቄ ሊቀርብላቸው ቀርቶ በተቃራኒው ዕድገትና የደመወዝ ጭማሪ አግኝተውበታል። የውጭዎቹም እስከረዳቶቻቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ አጋብሰውበታል። ይህ አሳዛኝ የሙያ ኪሳራ በየቀኑ በሃገራችን ፍርድ ቤቶች የምናየው ቲያትር ስለሆነ ሁኔታው ብዙ አይደንቅም።



6. የኤርትራና የኢትዩጵያ የካስ ኮሚሽን ውሳኔና የመንግስታቱ አቋም፤


ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ኮሚሽኑ የኢትዩጵያንና የኤርትራን የካሣ ይገባኛል ክርክር ከወሰነ ዘጠኝ አመታት አልፈዋል። ክርክሩ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት አስገዳጅና የመጨረሻ ነው። ጉዳዩን ለወሰነው ኮሚሽንም ሆነ ለሌላ አካል ይግባኝ ሊቀርብበት አይችልም። ሁለቱ ሃገሮች ከተስማሙበት ውጭ ወጥቶ የተወሰን ወይም መወሰን ሲገባው የታለፈ ጉዳይ ካለ እንደገና እንዲታይ አንዱ ውይም ሁለቱም ሃገሮች ኮሚሽኑን መጠየቅ ቢችሉም እስከ አሁን እንደዚያ ያለ ነገር ያነሳ ወገን የለም። ባጭሩ የካሣው ጉዳይ አልቆለታል።


የኮሚሽኑ ውሳኔ እንደታወቀ የኢትዩጵያም የኤርትራም መንግስት መግለጫ አውጥተዋል።


Image result for money  decisionsየኢትዩጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማይነት ባወጣው መግለጫ ኮሚሽኑ የኤርትራ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2 ፓራግራፍ 4 ን በመጣስ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ ባድመንና ሌሎች ወረዳዎች እንደወረረ ማረጋገጡን ካስታወሰ በኋላ የመጨረሻ የካሳ ውሳኔዎች በማሳለፍ ሥራውን ማጠናቀቁን ይገልጻል። በመቀጠልም ውሳኔው ብዙ ቴክኒካል ጉዳዩች እንድያዘ አትቶ በመግልጫው ዋና ዋናውቹን ብቻ እንደሚያነሳ ያመለከታል። በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ለኢትዩጵያ $ 174, 036, 520 ዶላር ለኤርትራ ደግሞ $ 161, 455, 000 ዶላር እንዲሁም ተጨማሪ $ 2, 065, 865 ዶላር በዜጎቹ ስም ላቀረበው ክስ እንዲከፈለው መወሰኑንም ይጠቅሳል። ለኢትዩጵያ እንዲከፈል የተወሰነው ካሣ በከፊል ኤርትራ በጠብ ጫሪነት በቀሰቀሰችው ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ለመካስ እንደሆነ ይናገራል። ለኤርትራ እንዲከፈል የተወሰነው ካሣ ወረራውን ለመመከት ኢትዩጵያ በወሰደችው እርምጃ የደረሰውን ጉዳት ለመካስ ነው ይላል። የካሳው ገንዘብ ሲቻቻል ቀሪው $ 10 000 000 ለሀገራችን የሚከፈል ሲሆን ከደረሰው ጉዳት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን ገልጾ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ዕቀባ ለመጣል እየተነጋገረ መሆኑ ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታካሂደውን አፍራሽ ተግባር ያሳያል ይላል። በመጨረሻም የሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት የካሳ ኮሚሸኑን ውሳኔ በዝርዝር እንደሚያጠና፤ ጥናቱም ኤርትራ የሚፈለግባትን ዕዳ እስድትከፍል ለማድረግ መውሰድ የሚቻለውን እርምጃ እንደሚጨምር በመግለጽ መግለጫውን ይደመድማል። የኢትዩጵያ መንግስት እስከአሁን ጥናቱን ጨርሶ በውሳኔው ላይ የያዘውን አቋም ባለመግለጹ ውሳኔውን እንዳለ እንደተቀበለ ይቆጠራል።

የኮሚሽኑን ወሳኔ በሚመለከት የኤርትራ መንግስትም መገለጫ አውጥቷል። በመግለጫው የድንበሩ ጉዳይ አልመቋጨቱ ቅር እንዳሰኘው ገልጾ የካሳውን ውሳኔ ግን እንዳለ እንደተቀበለው አመልክቷል። የኤርትራ መንግስት በወራሪነት ቢፈረጅም በአጠቃልይ ሲታይ መንግስታቸው እንደድንበሩ ጉዳይ የካሳውም ጉዳይ የተሳካለት ይመስላል። 14 ቢሊዩን ዶላር እንዲከፍል ተጠይቆ የሚፈለግበትን ገንዘብ ወደ 174 ሚሊዩን ማውረድ ችሏል። ይህ 174 ሚሊዩን ዶላር የኤርትራ መንግስት እንዲከለው ከታዘዘለት 163 ሚሊዩንዶላር ዕዳ ጋር የሚካካስ ነው። ቢሆንም የኢትዩጵያ መንግስት ለተመላሽ ኤርትራውያን ለመክፈል ቃል የገባው (ግምቱ 46  ሚሊዩን ት ገንዘብና ንብረት) ኤርትራ ወደብ ላይ ከቀረው ንብረት ( ግምቱ 117 ሚሊዩን ይሆነ ንብረት) ጋር ተደምሮ ወደ 160 ሚሊዩን ዶላር የሚጠጋ ኪሳራ በኢትዩጵያ ላይ ደርሷል። የኤርትራ መንግስት ባሳየው የላቀ ጥረትና ብልጠት ብራቮ ሊባል ይገባል። የኢትዩጵያ መንግስት ደግሞ በዚያው መጠን ሊነቀፍ ይገባል።




7. የካሣውን ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰላማዊ ሰዎች ማዋል

 
በካሣ የሚገኝን ገንዘብ ለህዝብ ጥቅም የማዋል የኢትዩጵያ መንግስታት ታሪክ አስደሳች አይደለም። ለምሳሌ የጣልያን መንግስት ለአምስቱ ዓመት ወረራ ጉዳት ለኢትዩጵያ መንግስት የከፈለው የካሣ ገንዘብ ለምን ተግባር እንደዋለ በብዙዎቻችን አይታወቅም። የምታውቁ ካላችሁ ብትነግሩን ደስ ይለናል። በጦርነት ወቅት የደረሰን ጉዳትን ለመካስ የተከፈለ ገንዘብን የሚመለከት ባይሆንም የኢትዩጵያ ወታደሮች ውጭ ሃገር ለሰጡት አገልግሎት የተባበሩት መንግስታት ወይም የውጭ መንግስታት የሚያደርጉት የገንዘብ ልገሳ ሁሌም ጦርነት ቀረሽ ጭቅጭቅ እንዳስነሳ ነው። የኮሪያና የኮንጎ ዘማቾች ለአገልግሎታችን ምስጋና ተብሎ ከውጭ የተላከ ገንዘብ በመንግስት ባለስልጣኖች ተበላ ብለው ለብዙ ዓመታት ሲያማረሩ አዲስ መንግስት በመጣም ቁጥር ሰልፍ ሲወጡ እናስታውሳለን። አሁን እያረጁና ቁጥራቸው እየተመናመነ ሲሄድ ጥያቄያቸውም እየተረሳ መጥቷል። በቅርቡም ከሩዋንዳ ይሁን ከኮንጎ የተመለሱ ሰላም ጠባቂዎች ከተመሳሳይ ምንጭ ከተገኘ ገንዘብ ድርሻችን ካልተሰጠን በማለት ሲያጉረመርሙ ትንሽ ትንሽ ጣል አድርገውላቸው ወደ ሥራችው እንደተመለሱ ይታወቃል።


Image result for Ethiopians displaced in Ethio-eritrea war የኢትዩጵያና የኤርትራ ካሣ ኮሚሽን ሊከፈል ይገባል ያለው ገንዘብ ለምን ተግባር መዋል እንዳለበት አልወሰነም። የመወሰንም ሥልጣን የለውም። የካሣው ጥያቄ በመንግስታት መካከል (interstate claim) ስሆነ ሁለቱ መንግስታት ገንዘቡን በነጻነት ላመኑበት ተግባር እንዲያውሉት የዓለም ዓቀፍ ህግ ይፈቅድላቸዋል። ኮሚሽኑ የመንግስታቱን አጉል ባህርይ ስለሚያወቅ ማናቸውም ገንዘብ እንዲከፈል ከመወሰኑ በፊት በደፈናው የገንዘብ ካሳ ክፍያ ቢወሰን ገዘቡን ለምን ተግባር ለማዋል እንዳሰቡ እንዲገልጹለት ሚያዝያ 2006 ላይ ጠይቋቸዋል። መንግስታቱ ለጥያቄው ሚያዝያ 2007 ላይ መልስ እንደሰጡት ኮሚሽኑ ነሓሴ 2007 “ስለ ጦር ጉዳቸኞች እርዳታ” በሚል ርዕስ ባሳለፈው ውሳኔ ቁጥር 8 ላይ ገልጿል። መንግስታቱ የሰጡትን መልስ ማወቅ ለሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች ጠቃሚ ነው። ቢያንስ መንግስታቱ ቃላቸውን እንዲያከብሩ ለመጠየቅ ይረዳቸዋል።

ኮሚሽኑ በውሳኔ ቁጥር 8 መግቢያ ላይ መንግስታቱ በጃቸው ያለውን resources በሙሉ ተጠቅመው በጦርነቱ የተጎዱ ወግኖቻቸው እርዳታ (relief) እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው እንደሚገነዘቡ እምነት እንዳለው ገልጿል። የኮሚሽኑ የሚያዝያ 2006 ደብዳቤ የሁለቱ መንግስታት የአልጀርሱን የታህሣስ 2000 ስምምነት አንቀጽ 5 (1) የሰብዓዊነት ዓላማ (humanitarian purpose) ማዕከላዊ ጉዳይ መሆኑን እንደሚረዱ ተስፋ በማድረግ የካሣውን ክፍያ ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰላማዊ ሕዝቦች እንዴት እንድሚያከፈፍሉ፤ ክፍፍሉን ለማድረግ በወቅቱ ስለነበሩና ወደፊት ስለሚኖሩ ተቋሞችና የአሰራር ዘዴዎች መረጃ እንዲሰጡት የሚጠይቅ ነበር። መንግስታቱ በመልሳቸው የስምምነቱን አንቀጽ 5 (1) የሰብዓዊነት ዓላማ እንደሚረዱ ገልጸው ኮሚሽኑ በጉዳዩ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጥ ይጠይቁታል። ኮሚሽኑ በተራው መንግስታቱ በካሣ መልክ እንዲከፈል በሚፈቀደው ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የመወሰን ሙሉ መብት እንዳላቸው አረጋግጦ መብቱን በሥራ ሲያውሉ የአንቀጽ 5 (1) የሰብዓዊነት ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ በማሳሰብ ይደመደማል።

የኮሚሽኑ የካሣ ክፍያ ገንዘብ አጠቃቀም ስጋት መንግስታቱ በሰጡት መልስ የተቀነሰ አይመስልም። የመጨረሻ የጉዳት ካሣ ክፍያ ውሳኔው ላይ እንደገና ይመጣበታል። ለምሳሌ ሴቶችን አስገድዶ መድፈርን በሚመለከት የኤርትራ መንግስት ድርጊቱ እንዲቆም በወታደሮቹና በሌሎች ላይ እርምጃ ባለመውሰዱ 2 ሚሊዩን ዶላር ካሣ ለኢትዩጵያ እንዲከፍል ተወስኖበታል። ይህን ገንዘብ የኢትዩጵያ መንግስት ጉዳቱ በደረሰበት አካባቢ ለሴቶች የሚሆን የጤና ፕሮግራም ለማዘጋጀትና ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያውለው ኮሚሽኑ ተስፋ እንደሚያደርግ በውሳኔው የመጨረሻ ክፍል ቁጥር 110 ላይ ገልጿል። የውሳኔው የመጨረሻ መስመር እንደገና የሚከፈለው ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰላማዊ ሰዎች እርዳታ መዋል እንደሚገባው በአጽንኦት ይገልጻል።

በካሣ መልክ እንዲከፈል የተወሰነው ገንዘብ ከኤርትራ መንግስት የሚመጣ ሳይሆን ዕዳው ተቻችሎ በኢትዩጵያ መንግስት እጅ የሚገኝ ነው። ይህ ገንዘብ፤ ገንዘቡ ከሌለም ከመንግስት ወጭ የሚሆን ተመጣጣ መጠን ያለው ገንዘብ በኮሚሽኑ ጥያቄ መሰረት በጦርነት ለተጎዱ ሰዎች መዋል ያለበት ቢሆንም ገንዘቡ ለተባለው ጥቅም እንደዋለ ወይም እንደሚውል ማስረጃ የለም። ከላይ እንደተመለከተው የካሣ ክርክሩ በመንግስታት መካከል የተካሄደ (interstate claim) ስለሆነ ጉዳቱ በመንግስት ላይ እንደደረሰ ተቆጥሮ የገንዘቡን አጠቃቀም ውሳኔ ለመንግስታቱ ተትቷል። ይህ አሰራር ያልተለመደ ባይሆንም እንደ ኢትዩጵያ ባለ መንግስት ለህዝብ ተጠሪነት በሌለበት ሃገር ጠቀሜታው አጠራጣሪ ነው። ገና ከመነሻው የካሣ ጥያቄው ሲቀብ ኮሚሽኑ አንዱ መንግስት ለሌላው ካሣ እንዲክፍል ከመወሰን ይልቅ በጦርነቱ ለተጎዱ ከለጋሾች እርዳታ ቢያፈላልግና ቢሰጣቸው እንደሚሻል የኢትዩጵያ መንግስት ጠይቆ ነበር። ኮሚሽኑ የኢትዩጵያ መንግስትን ጥያቄ ለማሟላት ስልጣን እንዳልተሰጠው ገልጾ ውድቅ አድርጎታል። እግረ መንገዱንም የኢትዩጵያ መንግስት በጦርነት የተጎዱትን ለመርዳት የሚያስፈልግ ገንዘብ በኤርትራ መንግስት እንዲከፈልኝ አልፈልግም ማለቱ የገንዘብ ካሣ ቢፈቀድለት ለተፈለገው ተግባር እንደማያውለው ጥርጣሬ ፈጥሮበታል። ከጦርነቱ በኋላ አንዳንድ የግንባታና የተፈናቀሉ ሰዎች የማቋቋም ሥራ መሰራቱ በህዝብ መገናኛ የተገለጸ ቢሆንም ሥራው ስለመሰራቱም ሆነ ስለአጥጋቢነቱ መናገር አይቻልም።




8.  በኤርትራ ላይ ብቻ የተጣለ የመሣሪያና ሌሎች ዕቀባዎች እና የማግለል ፖሊሲ፤ 


ኢትዩጵያና ኤርትራ በዓለም ካሉ የመጨረሻ የድሆች ሁሉ ድሆች ሃገሮች መደዳ የሚመደቡ ናቸው። የሁለቱ ሃገሮች መንግስታት ባካሄዱት ጦርነት በብዙ ቢሊዩን ዶላር የሚገመት ንብረት እና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር የሰላማዊ ሰዎችና የወታደሮች ህይወት ጠፍቷል። የአካል መጉደልና መቁሰል ደርሷል። መንግስታቱ ይህን ሁሉ የጥፋት “መስዋዕትነት” ሕዝቦቻቸውን ካስከፈሉ በኋላ ጦርነቱን ባስነሳው የድንበር ጉዳይም ሆነ በጦርነቱ ለደረሰ ጉዳት የተወሰነላቸው ካሣ እስከዚህ የሚያስደስት አይደለም።

Image result for Ethiopia and Eritreanከጦርነቱ በኋላ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የኢትዩጵያ መንግስት በወተደራዊ መስክ የኤርትራ መንግስት ደግም በድንበሩና በካሣው ውሳኔ ከጦርነቱ በፊት ከነበራቸው የተሻለ ቦታ ይዘዋል። ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሁለቱም አሸናፊ በሆኑበት መስክ እንደገፉበት ይገኛሉ። የኢትዩጵያ መንግስት በወታደራዊ ድሉ በመመካት የድንበሩን ውሳኔ ሙሉ ለመሉ አልፈጽምም ብሏል። የኤርትራ መንግስት በጦርነቱ በደረሰበት ሽንፈት የተነሳ ሌላ ጦርነት ውስጥ ገብቶ የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣል አይፈልግም። የኤርትራ መገንጠል ያለቀለት ጉዳይ መሆኑን  ብዙ ኢትዩጵያን የሚያምኑበት ቢሆንም የባህር በር (ወደብ) ጉዳይ ግን አሁንም አንገብጋቢና ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑን የኤርትራ መንግስት አይስተውም። ኢትዩጵያ ውስጥ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በጉልበት ይዞት ነው እንጂ የባህር በር (የወደብ) ፓለቲካ ምን ጊዜም ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ሊያመራ ይላል። በጦርነቱ ወቅት መፈረካከስ ጀምሮ የነበረውን የኤርትራ መንግስት ከመጥፋት በማዳን በወደቦቹ ላይ ይዞታውን ያረጋገጠለት የኢትዩጵያ መንግስት ነው። በጊዜ ብዛት ከሌላው የኤርትራ መሬት ተገድዶ ሊወጣ ቢችልም ቢያንስ የአሰብ ወደብን ይዞ መቆየት ባላስቸገረው ነበር። ሊያደርገው ግን አልፈለገም።

በግልጽ እንደሚታየው የተፈጠረው አዲስ ወታደራዊ የሃይል ሚዛን የማያስደስተው ቢሆንም የኤርትራ መንግስት ሊያናጋው አቅሙም ዝግጅቱም የለውም። አሁን ሙልጭ አድርጎ በመካድ አንዳንድ ኢትዩጵያንን ቢያሳምንም የሩቅ ተስፋው ኢትዩጵያ በውስጥ የፖለቲካ ችግር የተነሳ እንድትበታተንና መበታተኗን ተከትሎ በሚወጡት አምስት ወይም ስድስት አነስተኛ መንግስታት አዲስ ፖለቲካዊና ወታደርዊ የሃይል ሚዛን እንዲፈጠር ነው ብለው የሚያስቡ ኢትዩጵያውያን ጥቂት አይደሉም። ይህን እስትራተጂ እውን ለማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደሚሰራ ለማሳየት ብረት አንስተናል ለሚሉ የኢትዩጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችና የራሳቸውን መንግስት ማቆም ለሚፈልጉ የብሔር ድርጅቶች ሰፊ የገንዘብ፤ የወታደራዊና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ። ለዚህም መሳካት ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭትን ወደጎን በማድረግ የድንበሩን ውሳኔ እንዳለ ከማስፈጸም በስተቀር አልደራደርም ማለቱን ጨምረው ይገልፃሉ። በእኛ እምነት አሁንም ከአልጀርሱ ስምምነትና ዓለም ዓቀፍ ህግ አንጻር የኤርትራ መንግስት በድንበሩ ውሳኔ ላይ የያዘው አቋም ትክክል ቢሆንም የአንዳቸው ግትር አቋም ካልላላ በስተቀር ሁኔታው ባለበት መቀጠሉ አይቀርም። ይህ ሁኔታ ለሁለቱም ሃገሮች በተለይ ደግሞ ለኢትዩጵያ ጎጂነቱ አያጠያይቅም።

የጅቡቲና የኢትዩጵያ መንግስታት ያደረጉት ረዥምና የተወሳሰበ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአንዳንድ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ድጋፍ ታክሎበት ተሣክቷል። የስኬቱ ውጤት በኤርትራ መንግስት ላይ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ዕቀባ ማስጣሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሃገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደርዊ መሪዎች ከሀገር ውጭ እንዳይጓዙ፤ ገንዘብና ንብረታቸውንም እንዳያንቀሳቀሱ ታግደዋል። የዕቀባው ምክንያቶች ብዙ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ኤርትራ በአፍርካ ቀንድ የምትጫወተው አፍራሽ ሚና በተለይ በሱማሊያ ውስጥ ለጦርነት የምትሰጠው ድጋፍና ከጅቡቲ ጋር ያላትን የድንበር ችግር በሰላም ለመፍታት ፍላጎት አለማሳየቷ በዋናነት ይጠቀሳሉ። የዕቀባው ውጤት በተግባር እዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም በዲፕሎማሲው መስክ ለኤርትራ መንግስት ጥቃት ለጅቡቲና ለኢትዩጵያ መንግስታት ደግሞ ድል ሆኖ ይታያል። የጸጥታው ምክር ቤት ዕቀባ በኤርትራ ላይ እንዲጣል ብዙ የደከመው ኢትዩጵያ መንግስት አሁን እርቅ ሲፈልግ ዕቀባው ችግር እየፈጠረበት መጥቲል። እርቁን የምር ከፈለገ የተባበሩት መንግስታትን መርሳት ግድ ይሆንበታል፤ ማምረሩን ካዩ መንግሰታቱም አትታረቅ ብለው የሚያስቸግሩት አይሆንም።

የኤርትራ መንግስት እስከዚህ የሚያመረቃ የሰላምና የእርቅ ፍለጋ እንዲሁም የእቀባው ይነሳልኝ ትግል አላደረገም። ጥሩ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ማክበር ሪኮርድ የለውም። ሃገሩን ዘግቶ በተናዳፊ የውጭ ፖሊሲና ጊዜው ያለፈበት "በራስ የመተማመን" ገታራ የእድገት ስትራተጂ ከዚህም ከዚያም ጋር እየተላተመ ባለበት ይረግጣል። በኢትዩጵያ ላይ በቀጥታ በቀሰቀሰው ጦርነት ለህዝብ ህይወትና ንብረት ክብር አልሰጠም። ይህን ለሰዎች ህይወት ክብር አለመስጠት እስከ ቅርብ ወራት ድረስ ከሃገሩ ውጭ በሚያደርገው የእጅ አዙር ጦርነት ማዛመት ፍላጎት እያራመደው ይገኛል። አንዳንዶቸ እንደሚሉት ሳይሆን ብረት ላነሱ የኢትዩጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችና የብሄር ድረጀቶች የሚያደርገው ድጋፍ ሃገሪቱን ወደ ሰላምና ዲሞክራሲ ከመውሰድ ይልቅ ለእርስ በርስ ጦርነትና መበታተን እንደሚያዘጋጃት መገመት አይከብድም። በዚህ ጉዳይ "ሁኔታውን ለእኛ ተውልን። የኤርትራ መንግስት አንድነታችንና ብልጽግናችንን ይፈልጋል። ያለውን መንግስት ተረዳድተን እንጣል እንጂ መጪው ወቅት ብሩህ ነው"  የሚሉ ሰዎችን የሚጠራጠሩ በርካታ ናቸው። ሰዎቹ የሚሉትን እንስማ፤ ነገር ግን ችግሩ የሃገር ጉዳይ ስሆነ ለመላምታዊና ግምታዊ አነጋገር እንዲሁም ለሙከራና ለነሲብ አሰራር አይተውም። አነሰም በዛ ለዕቀባው መጣል እነዚሀ አፍራሸ የሆኑ የኤርትራ መንግስት ባህርያት አስተዋጸኦ ማድረጋቸው አጠያያቂ አይደለም። በዚሀ ሁኔታ ኢትዩጵያውያን በኤርትራ መንግስትና በመሪዎቹ ላይ የተጣለው ዕቀባ ባለበት እንዲቆይ ቢፈልጉ አይገርምም።

በሌላ ቢኩል ከኤርትራ መንግስት ባልተለየ ሁኔታ በኢትዩጵያ መንግስት ላይ የጦር መሳሪያ ዕቀባ፤ በከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ላይ ደግሞ የመዘዋወርና የገንዘብና ንብረት ማንቀሳቀስ እገዳ ሊደረግባቸው በተገባ ነበር። ለዕቀባው ምክንያቶቹ ለኤርትራ መንግስት ከተሰጡት ብዙ አይለዩም። የኢትዩጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነትና የዓለም ዓቀፍ ህግን ባለማክበር የድንበሩ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዳይፈጸም እምቢ ብሏል። ውሳኔው እንዳለ እንዲፈጸም ይወተውት ለነበርው የዓለም ዓቀፍ መህበረሰብም የሚገባውን ክብር አልሰጠም። የኤርትራ መንግስት እንደሚያደርገው ሁሉ ብረት ላነሱ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ድጋፍ ይሰጣል። በሃገር ውስጥ ደግሞ የህዝብን ዲሞከራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች አያከብርም። የኤርትራ መንግስት ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቢኖረው ኖሮ አሁን የደረሰበት ዕቀባ የሚጣለው በኢትዩጵያ መንግስትና መሪዎች ላይ በሆነ ነበር። ከዚህ ሃቅ አንጻር ሲታይ የኤርትራ መንግስት መጥፎ "ዲፕሎማሲ" እና ጨቌኝ የህዝብ አስተዳደር የኢትዩጵያ መንግስት ዓለም ዓቀፋዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድቶታል። አገር ውስጥም ስልጣኑን በእጅጉ እንዲያጠናክር አስችሎታል፤ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶችን ለማዳከምም ፋታ አግኝቷል።

በማናቸውም መለኪያ ቢታይ የኢትዩጵያ መንግስትና የኤርትራ መንግስት በጦርነት መሰል ፍጥጫ ላይ ያሉ ሀገሮች ናቸው። ስለወታደራዊ የሃይል ሚዛንና የኤርትራ መንግስት ከኢትዩጵያ መንግስት ጋር ቀጥታ ጦርነት አለመፈግ ያልነው እንደተጠበቀ ሆኖ በድንበሩ አካባቢ አንስተኛ ግጭት ቢነሳ ወደ ሰፊ ጦርነት የመለወጥ እድል አሁንም አለ። 




9. ምን ቢደረግ ይሻላል?



የኢትዩጵያም ሆነ የኤርትራ መንግስት አንዳቸው በሌላው ላይ ላደረሱት ጉዳት ካሣ እንዲከፍሉ በካሳ ኮሚሽኑ የታዘዘ ቢሆንም ትዕዛዙን ለመፈጽም አንዳቸውም የወሰዱት እርምጃ የለም። ምናልባትም አንዳቸው ከሌላው ላይ በካሳ መልክ የሚያገኙት ገንዘብ መጠን እዚህ ግባ የማይባል አነስተኛ ስለሆነ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን የካሳው ውሳኔ አፈጻጸም የአልጀርሱ ስምምነት አካል በመሆኑ እንደድንበሩ ውሳኔ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ባዩች ነን:: በዚህ አንጻር አንድ አሳሳቢ ነጥብ ቢኖር የኤርትራው ፕሬዚዳንት የካሳው ጉዳይ በኮሚሽኑ ውሳኔ ከተሰጠው በኋላ ከኢሳቴ (ESAT) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ከኢትዩጵያ ካሳ እንፈልጋልን የሚል ያልተጠበቀ አዲስ ነገር ማንሳታቸው ነው:: አጠቃላይ የንግግራቸውን ይዘትና የቃለ ምልልሱን ሂደት በማገናዘብ ይህ ጥያቄያቸው ከካሳ ኮሚሽኑ ውሳኔ ጋር ያልተያያዘ ከጦርነቱ በፊትና በኋላ ደረሰብን ለሚሉት ጉዳት እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው:: ነገርየው የድንበሩ ጉዳይ ከተፈታ በኋላ በሃገሮቹና በህዝቦቹ መካከል ግንኙነት እንዳይፈጠር አዲስ መሰናክል ሆኖ ብቅ እንዳይል ስጋት አለን:: ባጭሩ ቢታሰብበት ይበጃል ባዩች ነን:: 


ባላፉት በርካታ ዓመታት የኤርትራና የኢትዩጵያ መንግስታት ትኩረት በካሳው ጉዳይ ላይ ሳይሆን በድንበሩ ውሳኔ ላይ በመሆኑ በተለይ የትኛውን መሬት ማን ያገኛል የሚለው ሲያነጋግር ቆይቷል። ትክክልም ሆነ ስህተት የትግራይ ህዝብን እወክላለሁ የሚለው ህወሃት የድንበሩ ችግር ሲፈታ ድርጅቱ ለትግራይ በሚያስገኘው ወይም ለኤርትራ በሚለቀው መሬት ዓይንትና ስፋት መሰረት የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ሊቀጥልልኝ ወይም ሊያሽቅለቁልብኝ ይችላል ብሎ ሲያስብ ቆይቷል። ፍራቻው የሗለኛው እንዳያጋጥመው ነበር:: አሁንም ነው:: በተለይ ከጥቂት ወራት ወዲህ በፌደራል መንግስት ደረጃ የነበረው ከፍተኛ ድርሻ እየቀነሰ በመምጣቱ ፍራቻው እውን የመሆን እድል ስላለው ስጋቱ ቀላል አልሆነም:: ህወሃት በፌደራል ደረጃ ያለው ከፍተኛ ስልጣን ከመቀነሱ በፊት ሌላው የሃገሪቱ ህዝብ በድንበሩ ጉዳዩ ያገባዋል የሚል እምነት አልነበረውም::  አሁን ግን አማራጭ ስላጣ ችግሩን ለፌደራል መንግስት ወርውሮ የትግራይ ህዝብ መብት ጠባቂ በመምሰል ብቅ ማለት የሚፈልግ ይመስላል:: 

ሰሞኑን አዲሱ የፌደራል መንግስት መሪዎች የድንበሩ ቸግር ለዘለቄታው ተፈትቶ ኢትዩጵያውያንና ኤርትራውያን በሰላም እንዲኖሩና በጋር በኢኮኖሚም በሌላ መስክም እንዲበለጽጉ በመፈለግ የድንበሩን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ እንዳለ ተቀብለው እንደውሳኔው ለመፈጸም ተስማምተዋል:: ይህ ማለት የቀድሞ የሃገሪቱ መሪዎች ያቀርቧቸው  ያቀርቧቸው የነበሩ የንግግር ሰጥቶ መቀበልና የመሬት ሽግሽግ ጥያቄዎች አይነሱም ማለት ነው:: በግልጽ የሚታወቀው  የኤርትራ አቋምና ፍላጎት ይህ በመሆኑ ኢትዩጵያ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዳደረገች የሚረጋገጠው ከያዘቻቸው በድንበሩ ውሳኔ የኤርትራ የተባሉትን መሬቶች ለቃ ስትወጣ ብቻ ነው:: ከዚህ ባነሰ የሚወሰድ ማናቸውም እርምጃ የኤርትራን አዎንታ ካላገኘ በሰተቀር ውሳኔውን ያለቅድመሁኔታ እንዳለ እንደመፈጸም አይቆጠርም:: ከዚህ በፊት ለብዙ አኣመታት እንደታየው የኤርትራ አዎንታ አይገኝም:: የዚህ ሁኔታ ውጤት ተጨማሪ ጊዜ ማባከን ነው:: ጊዜ ባክኖም በመጨረሻ የሚለወጥ ነገር አይኖርም:: የኤርትራን ጽናት መረዳትና መቀበል ያስፈልጋል:: ህግም ሃቅም ስለማይደግፈን እያፈገፈግን  እያፈገፈግን የመጨረሻው አጣብቂኝ ላይ ደርሰናል:: ይለይልን::  

ህወሃት የድንበሩን ጉዳይ በኢትዩጵያ ህዝብ ላይ እንደተጫነ አላስፈላጊ ሸክም ሊያየውና የፌራል መንግስት የቀየሰውን የሁለቱን ሃገሮች ህዝቦች የሰላምና የብልጽግና አቅጣጫ በመደገፍ የሀገራችን ሰራዊት በውሳኔው የኤርትራ የተባሉትን መሬቶች ( ከተሞችና መንደሮች ጭምር) ለቆ እንዲወጣ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከከተሞችና ከመንደሮች ለሚፈናቀሉ ዜጎችቻችን   በቂ ካሳ መሬትና የንግድ ድርጅቶች በማቅረብ ሰፊ የማቋቋም ስራ መስራት ይገባዋል:: ህወሃት ይህን ሲያደርግ ብቻ ነው ብኝነት ለሁለት አስርት ዓመታት ያበላሸውን ሃገሮች ግንኙነት  መስመር ሊያስይዝ የሚችለው እንላለን::


ሰላም ለሁላችንም !! 

GLOBAL CONFLICT AND DISORDER PATTERNS: 2020

This paper was presented at the 2020 Munich Security Conference at a side event hosted by the Armed Conflict Location & Event D...